በሱዳን ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ ተጀመረ

ኢሳት (ታህሳስ 10 ፥ 2009)

የሱዳን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በሃገሪቱ ተፈጥሯል ያሉትን ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት በመቃወም ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞን ትናንት ዕሁድ ጀመሩ።

የፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር መንግስት በነዳጅ ላይ ሲያደርግ የቆየውን ድጎማ ካነሳ በኋላ በሱዳን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፈጠሩን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ይሁንና የተፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት መቃወም የጀመሩት ሱዳናዊያን በሃገሪቱ ባለው የሰብዓዊ መብት ዙሪያ ተመሳሳይ ቅሬታን ማቅረብ እንደጀመሩ ታውቋል።

የሱዳን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ እሁድ ከቤት ያለመውጣት አድማ እንዲጀመር ቅስቀሳ ማካሄዳቸውን ቢቢሲ ሰኞ ዘግቧል።

ይሁንና ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር የአድማውን ዘመቻ በመቃወም መንግስታቸው እየተካሄደ ባለው አድማ እንደማይወገድ ይፋዊ ምላሽን ሰጥተዋል።

በካርቱም የተጀመረው ከቤት ያለመውጣት አድማ ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ጭምር ያካተተ ሲሆን ወታደራዊ ቡድኖችም በዘመቻው መሳተፋቸውን አፍሪካን ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል።

በሃገሪቱ የተጀመረውን ከቤት ያለመውጣት ዘመቻ ተከትሎ የሱዳን መንግስት የደህንነት ሃይሎች በመገኛኛ ብዙሃንና በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ የእስር እርምጃን እየወሰደ መሆኑም ተመልክቷል።

በእስካሁኑ የመንግስት ዕርምጃ ከ40 የሚበልጡ የፓርቲ አባላት ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ መዲናይቱ ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ ግዛቶች ውጥረት መንገሱንም መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።

በአፍሪካ ለረዥም አመታት በስልጣን ከቆዩ መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ እየቀረበባቸው እንደሚገኝ ከህገሪቱ የሚወጡ ዘገባዎች የመለክታሉ።

ከ25 አመት በፊት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መሪ በመፍንቅለ መንግስት ድርጊት አስወግደው በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዚደንት አልበሽር በስልጣን ዘመናቸው የጦር ወንጀልን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ረገጣን እንደፈጸሙ ቅሬታ ይቀርብባቸዋል።

በተለይ በሃገሪቱ የዳርፉር ግዛት ፈጽመውታል በተባለ የጦር ወንጀል ፕሬዚደንቱ በአለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ተላልፎባቸው ይገኛል።