በሱዳናዊው የመኪና አሽከርካሪ ጥቃት የደረሰባት ኢትዮጵያዊት አረፈች

የካቲት ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የካቲት 24 ፣ 2007 ዓም በሱዳናዊ ሹፌር በአሰቃቂ ሁኔታ ጥቃት የተፈጸመባት ኢትዮጵያዊት ወጣት ማረፉዋን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ወጣቷ በአሰቃቂ ሁኔታ በጩቤ ተወጋግታ መሞቱዋን የገለጹት የወረታ ነዋሪዎች፣ ሹፌሩ በቁጥጥር ስር ውሎአል ቢባልም በትክክል ስላለበት ሁኔታ ማወቅ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ጭኖ ይጓዝ የነበረውን መኪና ሹፌር ወደ ባህርዳር እንዲወስዳት  እንፍራንዝ ከተማ ላይ ትብብር ጠይቃው ከፈቀደላት በሁዋላ፣ መንገድ ላይ የመድፈር ሙከራ ሳያድርግ እንዳልቀረና ይህን ተከትሎም ሆዷና ጎኗ አካባቢ በጩቤ ደጋግሞ በመውጋት፣ አይኖቿን በማውጣት ከመኪና ላይ ወርውሮ እንደጣላት የአይን እማኞች ይናገራሉ።

ድርጊቱ ሲፈጸም በሩቁ ያየ አንድ የሌላ መኪና አሽከርካሪ ቦታው  ደርሶ ወጣቷ ወደ ወረታ ለህክምና እንድትሄድ አድርጎ ድርጊቱን ለፖሊስ ሪፖርት ከማድረጉም በተጨማሪ፣ የሃሙሲት ህዝብ መረጃውን በመስማቱ መኪናውን ጠብቆ አስቁሞታል። በቁጣ ስሜት ውስጥ የነበረው የሃሙሲት ከተማ ህዝብ ሹፌሩን መደብደብ ሲጀምር፣ ፖሊሶች ጣልቃ በመግባት በደህንነት መኪና ተጭኖ ወደ ወረታ እንዲወሰድ አድርገውታል።

የሃሙሲት ከተማ ነዋሪዎች ግለሰቡ እዚሁ ፍርድ ማግኘት አለበት በማለት ቢጨቃጨቁም የሚሰማቸው እንዳላገኙ ለኢሳት ገልጸዋል። ዜናውን የሰማው የአካባቢው ህዝብ ቁጣውን ሲገልጽ ማምሸቱንም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የወጣቷ አስከሬን ወደ ትውልድ አካባቢዋ እንፍራንዝ ከተማ መመለሱን የአይን እማኞች አክለው ገልጸዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የሱዳን መኪኖች ማዳበሪያና ሌሎች እቃዎችን እየጫኑ መሃል አገር ድረስ ይገባሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ የወረታ ከተማ ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጠን ብንሞክርም ሳይሳካልን ቀርቷል።