ነኅሴ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተያዘው ክረምት በአብዛኛው ምስራቅና ሰሜን ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍሎች የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ የሰቆጣ ከተማና የአካባቢው ወንዞች በመድረቃቸው የውኃ እጥረቱ መከሰቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ነዋሪዎች ፣ በዝናቡ እጥረት የተነሳ የጉድጓድ ውሃ መጠን በማነሱ የሚጠጣ ውኃ እጥረት መከሰቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
“በከተማዋ በአጠቃላይ የውኃ ችግር ተከስቷል፡፡በከተማዋ የመጠጥ ውኃና ፍሳሽ ልማት ጽህፈት ቤት ምን እየሰራ እንደሆን አናውቅም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ የውሃ መስመሩ በየሳምንቱ ተበላሽቷል እንደሚባሉ ይናገራሉ፡፡ በየቤቱ የሚገኘው የቧንቧ መስመር አገልግሎት በመቋረጡ የሚጠጣ ውሃ ለማግኘት ከሌሊቱ አስር ሰዓት በመነሳት ወረፋ በመያዝ የገደል ውሃ ለመቅዳት መገደዳቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች በሌሊት ወጥተው እስከ ቀኑ አራት ሰዓት ድረስ አርፍደው ውሃ እንደሚያገኙ በምሬት ገልጸዋል፡፡
በከተማው ውስጥ ከፍተኛ የውኃ ችግር እንዳለ የሚገልጹት ሌላው የከተማ ነዋሪ ከዝናቡ መጥፋት ጋር ተያይዞ የሚታይ ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡በከተማው ውስጥ ለውስጥ የሚያቋርጡና በዙሪያው ያሉ ወንዞች መድረቅ ህብረተሰቡ ከወንዝ ቀድቶ መጠቀም እንዳይችል አድርጓል፡፡ዝናብ አንድ አንድ ጊዜ ሲዘንብ እንዲህ ያለ መጨናነቅ እንደማይከሰት የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢ አልፎ አልፎ በሚጥለው ዝናብ ከቆርቆሮ ላይ በመሰብሰብ የየዕለት ችግራቸውን ለመቅረፍ እንደሚሞክሩ ይናገራሉ። ዝናብ በወር አንዴ ብቻ መዝነቡንና ከዚህ ውጭ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የሚቆይ ካፊያ ብቻ መሆኑ የውኃውን ችግር እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡
የከተማዋ አስተድደር ከአሁን በፊት ውኃ በቦቲ በማቅረብ የህዝቡን ጊዜያዊ ችግር ለመቅረፍ ቢሞክርም፣ አሁን አገልግሎቱ በመቋረጡ የከተማው ህዝብ በችግር ላይ ነው፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚናገሩት በነሃሴ ወር ከአሁን በፊት እንደዚህ ዓይነት የውኃ ችግር ተከስቶ እንደማያውቅ ተናግረው፤አልፎ አልፎ በሚጥለው ዝናብ የደረቀውን መሬት ከማራስ አልፎ ወደ ከርሰ ምድር የሚዘልቅ ውኃ ባለመኖሩ ከመስከረም ወር በኋላ ከፍተኛ የውኃ ችግር ሊከሰት ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳላቸው አክለዋል።
የገዢው መንግስት አመራሮች ምንም አይነት ትኩረት ባለመስጠታቸው ህብረተሰቡ ለከፍተኛ የውሃ ችግር መጋለጡን የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ የጉድጓድ ውኃ ለመቅዳት በወረፋ ሰበብ ህዝቡ እርስ በርሱ ሲጣላ እና ቀኑን ሙሉ አንድ ጀሪካን ውኃ ለመቅዳት ተሰልፎ ስራ ሲፈታ በዝምታ ከማየት ሌላ የፈየዱልን የመፍትሄ ነገር የለም በማለት ይናገራሉ፡፡
ከአሁን በፊት ለሃያ አመታት ያገለግላል ተብሎ በከፍተኛ ወጪ የተሰራው የቧንቧ ውኃ ፣ ሶስት ዓመት ብቻ አገልግሎ ደርቋል።