ሚያዚያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በጨርቆስ ክፍለከተማ በተካሄደው ምርጫ ከፍተኛውን ዘለፋና ትችት ያስተናገዱት ወ/ሮ አዜብ መስፍን እና ባለራእዩ ባለቤታቸው እንደነበሩ በቆጠራው የተሳተፉ የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።
ኢሳት በ8 የአዲስ አበባ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የተሳተፉ ታዛቢዎችን በመጠየቅ ባሰባሰበው መረጃ ከ30 በመቶ ያላነሰ መራጭ ድምጹን የሰጠ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ባዶ ወረቀት ሲያስገቡ፣ አብዛኞቹ ደግሞ ከዘለፋ ጀምሮ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን ጽፈው አስገብተዋል። እንደ ታዛቢዎች መረጃ አብዛኞቹ ስድቦች በወ/ሮ አዜብ መስፍንና በባለቤታቸው ላይ ያነጣጠሩ ሲሆን፣ ስድቦቹም በአብዛኛው ወ/ሮ አዜብን በሙስና የሚከሱ ናቸው።
የአዲስ አበባ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ እንደቀበራቸው እና ከፍተኛ የህዝብ ፍቅር እንዳላቸው በመንግስት መገናኛ ብዙሀን የተነገርላቸው አቶ መለስ ዜናዊም ትችቱ አልቀረላቸውም። በእሳቸው ላይ የተሰነዘረው ዘለፋና ትችት ባለራእይነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እንደነበር የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
መራጮች በጻፉዋቸው መልክቶች የተደናገጡት የምርጫ ቦርድ እና የቀበሌ ባለስልጣናት በ ወረቀቶቹ ላይ ስለሚወስዱት እርምጃ ግራ ተጋብተዋል።
በ ምርጫው መላው ኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ቃል ኢህአዴግን እንደማይደገፍ ግልጽ ማድረጉን ታዛቢዎች ይገልጻሉ።
ኢሳት ከወራት በፊት ለምርጫው የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ከተጠበቀው በታች መሆኑን መዘገቡ ይታወሳል።