ኢሳት (የካቲት 21 ፥ 2008)
በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ለሁለተኛ ቀን ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ቀጥሎ መዋሉን እሳት ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጹ።
ተቃውሞው ከተቀሰቀሰ በኋላ በወረዳዋ ባለስጣናት መካከል ውዝግብ መፈጠሩም ከውስጥ ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ተከትሎ የዳባት ወረዳ የደህንነት ሃላፊ፣ የሚሊሺያ ዘርፍ ሃላፊና፣ የሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤት ሃላፊ መታሰራቸውን ከስፍራው የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
በዛሬው ምሽት ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚያገናኙ መንገደችም በህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪዎች መዘጋታቸው ታውቋል። በደባርቅ ከተማም ተኩስ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፣ በዳባት ወረዳ አጎራባች መንደሮች ላይ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ መጀመሩን ማምሻውን ኢሳት በስልክ አረጋግጧል።
ህዝቡ በአሁኑ ሰዓት በዋነኝነት የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርድ፣ ወደትግራይ ክልል የተካለሉት ወልቃይት ጠገዴ እና ጸለምት ወደቀድሞ ማንነታቸው እንዲመለሱና፣ እውቀት የሌላቸው የወረዳው ባለስልጣናት ህዝቡን ሊመሩ አይችሉም የሚሉ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።