በሰሜን ጎንደር የአርባ ፀጓር ፀባሪያ ነዋሪዎች ባለፉት ሃያ አራት ዓመታ ውስጥ ብአዴን ምንም እንዳልሰራላቸው ተናገሩ

ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተከዜ ወንዝ ጫፍ ላይ የምትኘውና የዋግና የበለሳ ነዋሪዎች መተላለፊያ የሆነችው አርባ ፀጓር ወረዳ ደርግን ለመጣል በተደረገው የትግል ወቅት የኢህአፓና የኢሕዲን መተላለፊያ መስመር የነበረች ሲሆን በወቅቱ የድሮው ኢሕዲን የአሁኑ ብአዴን ታጋዮች የነበሩት ለሕዝቡ የኑሮ ለውጥና ዴሞክራሲያ ስርዓት እንደሚገነቡ ቃል በመግባታቸው ነዋሪው ሸማቂዎቹን በማገዝ ከለላ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን ድል አድርገው መንበረ ስልጣኑን ከያዙ በኋላ ግን ቃላቸውን በማጠፍ ምንም የልማት ስራዎች እንዳልተሰራላቸው ነዋሪዎቹ ምሬታቸውን ገልፀዋል።
በቀበሌው ነዋሪዎቹ የተነሱ አሳዛኝ ልብ ሰባሪ ጥያቄዎች፣ አብዛኛውን ታዳሚ ያስለቀሱ ሲሆን ለአስራ አንድ ዓመታት አርባ ፀጓር ፀባሪያ ቀበሌን በሊቀመንበርነት የመሩት የአካባቢው ነዋሪ እንዳሉት ”“በዚህ አካባቢ አንዳንድ ውርውር ከሚሉ ቆርቆሮዎች በስተቀር በልማት ተጠቃሚ ነን ብሎ መናገር አይቻልም። ለምን ከተባለ፣ እኛ የደም ዋጋችንን ስጡን እያልን ሳይሆን፣ ሌላው ሕብረተሰብ እንደሚያገኘው ከልማቱ ተጠቃሚ እንሁን ነው ጥያቄያችን። እንደሚታወቀው ደርግን ስንጥል ችግራችን ሁለት ዓብይ ነገሮች ነበሩ። አንዱ ራሱ ደርግ ነበር። ሁለተኛው ግን የተፈጥሮ ድርቅ ነበር። ሁለቱንም አጣምረን ደርግን መጣል ችለናል። ”

አክለውም አሉ ”አሁን ላይ ግን በዚህ አካባቢ ያለነው ነዋሪዎች እየሳሳን መጣን። ከመብራት ርቀናል፣ ከውሃ ርቀናል። በተለይ በውሃ ምክንያት ልንበታተን ነው። ከፊላችን ወደ ተከዜ፣ ከፊላችን ወደ መና ልንበታተን ነው። የምንጠጣው ውሃ የለም። የምንጠጣው ውሃ የከበት ሽንት ነው። ይህችን የምትመለከቷት ት/ቤት እንኳን በሕብረተሰቡ ተሳትፎ የተሰራ ነው። እኛው እራሳችን ነን የሰራነው፣ ሌላ ማንም የለም። በመንግስት የተደረገልን እገዛ የለም። ከጤና አንፃር ሕክምና ለማግኘት ስልሳ ኪሎ ሜትር አቆራርጠን ሄደን ነው የምንጠቀመው። ” ሲሉ አሳስበዋል።
ሁለተኛ ተናጋሪ የነበሩት በትግሉ ወቅት ቤተሰባቸው ያጡ አዛውንት ወ/ሮ ክቤ ዳዊት ሲሆኑ እንዲህ በማለት ነበር ምሬታቸውን የገለጹት ”ደርግን ለመጣል ወንዱም ሴቱ እኩል ነው የተዋጋነው። ደርግን አምርረን ነበር የታገልነው። ከድል በኋላ ግን ኢሕአዴግ ከፍ ሲል፣ እኛ ቀያችንን ያለቀቅነው ግን ችግራችን አልተፈታም። የውሃ ጥሙን፣ የኑሮው መራራነቱን አልቻልነውም። አካባቢያችን በተፈጥሮም የተጎዳ ነው። እስካሁን ድረስስ ዳዋውን ገደሉንም እየጣስን፣ የሚበላም እንጀራም ስለነበረን ግድ ውሃ ስናመጣ ነበረ። አሁን ግን ከመስከረም ጀምሮ ውሃው መራራው ባሰን። የምናመጣው ውሃ ቆሻሻ ነው። ስለውሃው ብናወጋ ደስ አይልም። እየጠላነውም ስለምንጠጣው በታይፎይድ በሽታ ትልቁም ትንሹም ተጠቅቷል። መሮናል፣ ቅጡ መሄጃው ጠፍቶን ነው። ሁል ጊዜ ውሃ፣ ሁልጊዜ ጤና ቸገረን፣ ነፃ ከሆንን እንኳን መንግስቱ እንዴት አይተባበረንም? የማያውቁትስ የማያውቁ ሆነው ነው። እዚህ ከእኛ ጋር በትግሉ ጊዜ የነበሩ የእኛን ችግር እንዴት ረሱት? ያውቁት የለ እንዴ? ርሃብን ጥማቱን እንግልቱን። ”

”ያን ሁሉ መከራ ቆሎ ተሸክመን፣ ጥይት ተሸክመን የኖርን ሰዎች፣ እንዴት ጤና ጣቢያ እንከለከላለን? ወተቱንም፣ ስጋውንም ያለቀን እርጎ ደብልቀን በደህናው ጊዜ በዋንጫ ተይዞ እነሆ ስለስላሴ እየተባለ በልተን ጠጥተን ነበር። ዛሬ ነፃነት ሲገኝ ግን ዞረው አለማየታቸው በጣም ያሳዝናል። ትግሉ ሲያበቃ፣ ሁሉንም ነገር ታገኛላችሁ እንደተባልነው አይደለም። ውሃና ጤና ከሌለ ሰው እንዴት ሰርቶ ሊበላ ነው? እያለቀስን፣ እያዘንን ነው የምንኖረው። ካልሆነም ደግሞ ወደ ደህና አገር ብትሰዱን እንሄዳለን። ጤና ካለ የሚበላ ካለ ስደዱን፤ ሁሉም ሀገራችን ነው ሄደን እንኖራለን። አባቶቻችን እዚህ አስቀመጡን እኛም የሰው ኩሌታ ልንሆን ነው። ልጆቻችንም በችግር ውስጥ እየተተኩ ነው። በወቅቱ የታጋይ ልጆች የነበሩ በረንዳ አዳሪ ሆነው ቀርተዋል። ሴቶቹ ሴተኛ አዳሪ ሆነዋል። አባት የሌለው ልጅ ማን ያስተምረዋል? ትንሽ ያላቸው ሰዎች ነው ወደላይ የተንጠላጠሉት። የሟች ልጆች ግን ወድቀው ነው የቀሩት። እያየናቸው እያለቀስን ነው የምንኖረው። አባቶቻችሁ ቢኖሩ ጥሩ ኑሮ ትኖሩ ነበር። ትማሩም ነበር፣ እያልን እያለቀስን እንኖራለን። አካባቢያችን ከችግር አልወጣም። ሌላው ቢቀር ለእባብ የምትከላከል ጤና ጣቢያ እንኳን ስሩልን።
ሲሉ ተማፅኖዋቸውን ያሰሙ ሲሆን በተጨማሪም አሉ ”ያ ሁሉ ያወጋነው የትሄደ? አብረን የበላነው፣ አብረን የጠጣነው የት ሄደ? እንዴት ችግራችንን አይነግሩልንም? ሌላውስ ቢሆን በልማት እንዲህ አመረተ… ሲባል እንሰማለን። ሀገር ሁሉ ግን አንድ አይነት አይደለም። አካባቢያችን በተፈጥሮ ለችግር የተጋለጠ በመሆኑ መንግስት አላገዘንም ብለን እናማለን” ሲሉ ተማፅነዋል።
ለወ/ሮ ክቤ ዳዊት “ያ ሁሉ ያወጋነው የት አደረሳችሁት? የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር። ያወጋችሁት ወጎች ምን ነበሩ?” ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ
”ካወጋናቸው ወጎች አንዱ የነበረው፤ ደርግን ጥለን የዴሞክራሲ፣ የሠላም እና አንድ አይነት ኑሮ እንኖራለን ብለን መክረን ነበር። የተማረውም ያልተማረውም በአንድ ላይ ተጠርንፈን በእኩል እንኖራለን ተብሎ ነበር፤ እንደሌሎቹ መማር የምንችል የነበርነው ዛሬ ግን ያልተማርነው ባዷችን ቀርተናል”ማለታቸውን ሰንደቅ ጋዜጣ ባሳለፍነው ሳምንት ዘግቧል።