ታኀሳስ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ገዢው ፓርቲ ሆን ብሎ እንዳስነሳው በሚነገረው ግጭት በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል። በአማራና ቅማንት ህዝብ መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነትና ዝምድና በማፍረስ አካባቢውን ወደ ግጭት ለመቀየር ገዢው ፓርቲ አስታጥቆ ያሰማራቸው ሚሊሺያዎች ግድያ እየፈጸሙ መሆኑን ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል። እንዲህ አይነት ድርጊት ተፈጽሞ አያውቅም የሚሉት ነዋሪዎች ግጭቱ እየተስፋፋ የተለያዩ ወረዳዎችንና ቀበሌዎችን እያካተተ መምጣቱን ገልጸዋል። ነጋዴ ባህር፣ ጮንጭቅ፣ ብሆና፣ ጉባይ በተባሉት አካባቢዎች አሁንም ድረስ ግጭት አለ። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ግጭቱ ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ ከ50 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ቢገልጹም፣ ኢሳት የተጠቀሰውን አሃዝ ከሰሜን ጎንደር ፖሊስ ጽ/ቤት ለማረጋገጥ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም።
ትናንት ምሽት ጭልጋ ጮንጭንቅ በሚባለው አካባቢ የመንግስት ታጣቂዎች መኖሪያ ቤቶችንና የስብል ክምር አቃጥለው ሲሮጡ፣ ገበሬዎች ተከታትለው በታጣቂዎቹ ላይ ተኩስ ከፍተዋል። ግጭቱ ይህን ዜና እሳካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አልበረደም። በአርማጭሆም ልዩ ሃይሎች ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም እየተዘጋጁ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። ልዩ ሃይሎች ከትክል ድንጋይ ትምህርት ቤት ጀርባ ባለ ተራራ ላይ መትረጊስ ጠምደው በመታየታቸው ተማሪዎች አንማርም ብለው ትምህርት ቤቱን ለቀው ወጥተዋል። ሽንፋ ላይ ደግሞ ታጣቂዎቹ ሰዎችን ከቤት እያስወጡ ንብረታቸውን ዘርፈዋል።