በሰሜን ጎንደር የተለያዩ ፖለቲካዊና ማኀበራዊ ይዘት ያላቸው መፅሔቶችና መፅሐፎች እንዳይሸጡ ታገደ

የካቲት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፍኖተ ነጻነት እንደዘገበው  መጽሄቶችንና መፅሀፎችን አዙረው የሚሸጡ  ወጣቶችም ከየካቲት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ  የያዙዋቸው መጽሀፎችና መጽሄቶች ተወርሶባቸዋል።

በተለይ በጎንደር ከተማ ቀበሌ 11 ልዩ  ስሙ አባጃሌ በሚባል አካባቢ ያሉ የደንብ  አስከባሪዎች እዚህ ጎንደር ውስጥ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን   መፅሔቶች፣ ጋዜጦችና መፅሐፎች  መሸጥ አትችሉም በሚል በተደጋጋሚ  ጊዜ ከአዙሪዎች እየወረሱ ቅጣት እያሉ   ያስከፍሏቸው እንደነበር ቢታወቅም   የካቲት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ግን ሙሉ   በሙሉ እንደወረሱባቸው ተዘግቧል።

 

በአካባቢው ጋዜጣ፣ መፅሔትና መፅሐፍ   እያዞሩ ከሚሸጡት ወጣቶች መካከል  አብዛኞቹ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ተመርቀው ስራ አጥ የሆኑ እንደሆነም ጋዜጣው ዘግቧል።

ወጣቶቹ የተወረሱባቸውን ንብረቶች   ለማስመለስ ወደ አካባቢው መስተዳደር   ስራ አስኪያጅ ቢያመሩም ሥራ አስኪያጁ   “የተወረሰባቸው የወጣቶቹ ንብረት   ሊመለስ ይገባል  ወንጀል እስካልፈፀሙ   ድረስም አዙረው መሸጥ ይችላሉ” ቢሉም   የደንብ አስከባሪዎቹ ለመመለስ ፈቃደኛ   አልሆኑም።

የደንብ አስከባሪዎችም የአካባቢውን   የብአዴን/ኢህአዴግ የድርጅት ጉዳይ  ኃላፊ የሆኑት አቶ አያና ካልፈቀዱ   አይመለስላቸውም ያሉ ሲሆን አቶ አያናም  የተወረሱት መሔቶችና መፅሐፎች   እንዲወረሱ ትዕዛዝ መስጠታቸው ታውቋል፡፡  ወጣቶቹም በሁኔታው እጅግ ከማዘናቸው   በተጨማሪ “ጋዜጦች፣ መፅሔቶችና   መፅሐፎቹ የሚታተሙት አዲስ አበባ   የመንግስት ኃላፊዎች በሚያውቁት ህጋዊ መንገድ ሆኖ ሳለ ጎንደር እየመረጡ አትሽጡ   መባላችን ምክንያቱ አልገባንም፣ የጎንደር  ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያ ህዝብ ተለይቶ  የሚታተሙ ህጋዊ ፅሑፎችን አታንብቡ፣  መረጃም አታግኙ እንደማለት ይቆጠራል፤  እኛንም ሰርታችሁ አትብሉ እንደማልት ነው”  ሲሉ ያላቸውን ቅሬታ ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡

በከተማው ያነጋገርናቸው እንዳንድ  አንባቢዎች በበኩላቸው “በተለይ በጎንደር  የኢህአዴግ ባለሥልጣናት በሚፈፅሙት   ሙስና እና ብልሹ አሰራር በህዝቡ ላይ ከፍተኛ   ጫና ፈጥሯል፡፡ ህዝቡ መረጃ እንዳያገኝ   ማድረጋቸውም አዲስ አይደለም፤ ይህም ህዝቡ   ላይ ከፍተኛ ቁጣን እየቀሰቀሰ መሆኑ ግልፅ   ነው” ሲሉ በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡

 

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአካባቢው የፀጥታ  ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አዶዬ እንየውን  ስለሁኔታው ጠይቀናቸው ወጣቶቹ መንገድ ሳይዘጉ እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው መሸጥ  እንደሚችሉና ማንም ሊወርስባቸው  እንደማይችል በመግለፅ ስለመወረሱም  የሚያውቁት መረጃ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡

የአካባቢው የብአዴን/ኢህአዴግ ድርጅት  ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ አያናን  የወጣቶቹን ንብረት እንዲወረስ እንዳደረጉ  ብንጠይቃቸውም ለፍኖተ ነፃነት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

 

በትግራይ መቀሌ ከተማ መጽሄቶችንና ጋዜጦችን በማዞር ሲሸጡ የነበሩ ወጣቶች ተይዘው መጽሄቶቻቸው እና መጽሀፎቻቸው እንደተወረሱባቸው መዘገባችን ይታወሳል።

 

በተያያዘ ዜናም በዋነኝነት መቀመጫውን ጣሊያን ሀገር   ላደረገና ንብረትነቱ የጣሊያናዊ ለሆነ    “አሳማን” ለሚባል ድህረ-ገፅ የሚፅፈው   ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ በተደጋጋሚ

ጊዜ የኢትዮጵያ የደህንነት ኃይሎች   የጋዜጠኝነት ስራውን እንዲያቆም    ማስፈራሪያና ዛቻ ይፈፅሙበት እንደነበርና    በቅርቡም የግድያ ዛቻ እንደደረሰበት ፍኖተ ዘግቧል፡፡

በተለይ የግድያው ዛቻ የተፈፀመበት   ጥር 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ በ 7፡   51 ሰዓት፤ በድጋሚ ደግሞ ጥር 20 ቀን  2005 ዓ.ም. ከቀኑ በ 10፡05 ሰዓት ላይ ሲሆን፣

ከዚህ በኋላ አንተን ማሰር አያስፈልግም   አሁን በማንኛውም ጊዜ ማስወገድ የሚለውን    የተሻለ ሆኖ አግኝተነዋል ሲሉ እንደዛቱበት   ለጋዜጣው ዘጋቢ ተናግሯል።

በተደጋጋሚም እራሳቸውን የደህንነት   ኃይሎች እንደሆኑ በመግለፅ “እያንዳንዷን   ስራህን እናውቃለን፣ ለማን እንደምትሰራም   እንዲሁ፤ ስላንተ ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን”   በማለት የሐሰት ውንጀላ ለማድረግ መንገድ   እየጠረጉ መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡   ለዚህም ዋነኛ ምክነያት ያደረጉት   ፅሑፎቹ በቋሚነት ከሚፅፍባቸው ድህረ-  ገፆች ተወስደው ኢህአዴግ አሸባሪ ሲል  በሰየመው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ   ግንባር(ኦብነግ) ድህረ-ገፅ ላይ በመታየታቸው እኔ ሆን ብዬ ለኦብነግ እንደፃፍኩ   ለማስመሰል እየተሞከረ ነው፡፡ ነገር ግን  የኦብነግ ጋዜጠኞች እንደማንኛውም  የዓለማችን ጋዜጠኛ የሚፈልጉትን መረጃ መርጠው መውሰድ እንደሚችሉ  ጠፍቷቸው አይደልም፤ ይልቁንም ሆን  ብለው የሐሰት ውንጀላ ለመፈፀም አስበው  የሚያደርጉት እንጂ እኔ ከኦብነግ ጋር ምንም የሚያገናኘኝ ነገር የለም ብሏል ጋዜጠኛ በትረ፡፡

ጋዜጠኛው ተቀጥሮ ከሚሰራበት “ አሳማን”   ድህረ-ገፅ በተጨማሪ ያለምንም ክፍያ   በፈቃደኝነት “ዘ ደይሊ ጆርናሊሰት” እና   የራሱ ድህረ-ገፅ በሆነው “ ኢትዮጵያ ሆት

ዶት ወርድ ፕሬስ” ላይ በተለያዩ   ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚፅፍ ይታወቃል፡፡