በሰሜን ጎንደር የሚደረጉ ውጊያዎችን በገዢው ፓርቲ በኩል ሆነው ሲመሩ የቆዩት የዞኑ የልዩ ሃይል አዛዥ ኮማንደር ዋኘው አዘዘው መታሰራቸውን ምንጮች ገልጹ።

ታኅሣሥስ ፫ (ሦስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ኮማንደሩ ትናንት ምሽት ተይዘው ፣ በወታደራዊ እዙ (ኮማንድ ፖስት) የሚታሰሩ ሰዎች ወደ ሚገኙበት ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል።

ኮማንደሩ ጦራቸውን ይዘው ተሰውረዋል እየተባለ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘገብ ቆይቷል። የኮማንደር ዋኘው ደጋፊዎችንና በእሱ ስር ያሉ ወታደሮችን ለመያዝ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ምንጮች ገልጸዋል። እርምጃው በህወሃት በሚመራው ወታደራዊ እዝ ( ኮማንድ ፖስት) እና በክልሉ ልዩ ሃይል መካከል ያለውን ልዩነት እያሰፋው እንደሚሄድ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከነጻነት አርበኞች ጋር በተደረገው ጦርነት በገዢው ፓርቲ በኩል ለደረሰው ከፍተኛ ሽንፈት ኮማንደሩ ተጠያቂ ሆነዋል። በአርማጭሆ፣ በደባትና ወገራ በተደረጉት ተከታታይ ውጊያዎች ገዢው ፓርቲ ከ100 በላይ የሚሆኑ ወታደሮችን አጥቷል።

የሰሜን ጎንደር  ዋና ማረሚያ ቤት ሃላፊ ኢንስፔክተር ልጃለም መሰረት መታሰራቸውንም ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል። ኢንስፔክተሩ ኮ/ል ደመቀ ዘውዴን በካቴና ታስረው ፍርድ ቤት እንዳይቀረቡ አድርገዋል በሚል ሰበብ ከታሰሩ በሁዋላ፣ ጉዳያቸውን የሚያይላቸው ባለስልጣን በመጥፋቱ ለፌደራል ባለስልጣናት ደብዳቤ እስከመጻፍ ደርሰዋል።