ታኅሣሥ ፲ (አሥር)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- “ከአምባጊዮርጊስ እስከ ደባት መሽገው የሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ አግባቡልን” በማለት የህወሃት/ኢህአዴግ ካድሬዎች በ31 ቀበሌዎች ስብሰባ አድርገው በእያንዳንዱ ቀበሌ 30 ሽማግሌዎችን አስመርጠዋል ። ካድሬዎች፣” እኛ አንድ ሺ ወታደር ቢገደልብን ሌላ አንድ ሺ እናመጣለን፣ አንድ አርሶአደር ቢገድል ግን አይተካም” የሚል ቅስቀሳ የጀመሩ ሲሆን፣ የነጻነት ታጋዮቹ በበኩላቸው፣ ማንኛውም ሽማግሌ፣ የሃይማኖት አባትም ሆነ ሌላ ግለሰብ፣ ሽንፈት እየደረሰበት ያለውን አገዛዝ ለመታደግ እነሱ ወዳሉበት አካባቢ ከመጣ እርምጃ ይወስድበታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“ ከበብኳቸው ሲል አያገኘንም፣ ወጡ ሲል እንመጣበታለን” የሚሉት ታጋዮቹ፣ ሽንፈት ሲደርስበት በሽማግሌ ለመፍታት የሚያደርገውን ሙከራ አንቀበልም ፣ እኛ የህይወት መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን” ብለዋል። የሚላኩት ሽማግሌዎች ይህን አውቀው አርፈው እንዲቀመጡ፣ ካልተቀመጡ ግን እርምጃው በማንኛውም ጊዜ ይወሰዳል ብለዋል።
“ሽምግልናው የተስፋ መቁረጥ ምልክት ነው” የሚሉት ታጋዮች፣ ከእነሱ ጋር እንዲዋጉ የሚላኩት ለጋ ወጣቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል። ህዝቡም ከታጋዮች ጎን ተሰልፎ ትግሉን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።