በሰሜን ጎንደር ዞን በሮቢት ከተማ አካባቢ በሚካሄደው ውጊያ ነዋሪዎች መጎዳታቸው እንዲሁም የአገዛዙ ወታደሮች መገደላቸው ታወቀ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ/ም) ዛሬ፣ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓም ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሮቢት ከተማ አካባቢ በሚገኙ የገጠር የቀበሌዎች፣ አገዛዙ በከባድ የጦር መሳሪያዎች የታጀበ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት አሰማርቶ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ ከወታደሮች በኩልም 7 ተገድለው 2 መማረካቸው አርበኞች ግንቦት7 የላከልን መረጃ ያመለክታል። አንድ የአካባቢው ሽማግሌ ቦንብ ተወርውሮባቸው ህይወታቸው ማለፉንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ወታደሮቹ በህዝብ ላይ ከባድ መሳሪያዎችን መጠቀማቸውን የገለጸው ንቅናቄው፣ ህወሃት በላይ አርማጭሆ ገንበራ በተባለው ቀበሌ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር እያስገባ ሲሆን፣ ህዝቡም ከአርበኞች ጎን በመሰለፍ እየተፋለመ ይገኛል ብሎአል። በአካባቢው የስልክ መስመር ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑንም ንቅናቄው አክሎ ገልጿል።
ኢሳት በበኩሉ ባደረገው ማጣራት ዛሬ በግምት ከ 3 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት በተደረገው ውጊያ 4 ወታደሮች ሲገደሉ 7 ደግሞ ቆስለዋል:: 7 ክላሽንኮፍ የጦር መሳሪያዎች ተማርከዋል::
ህወሃት መራሹ አገዛዝ የአካባቢውን ህዝብ የጦር መሳሪያ ለማስፈታት እንደ አዲስ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ሙከራ ሲያደርግ በወታደሮቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ነበር።