በሰሜን ጎንደር ዞን በርካታ የልዩ ሃይል አባላትና ሰላማዊ ዜጎች ተገደሉ

ጥቅምት ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከቅማንት ብሄረሰብ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአርሶ አደሩና በክልሉ ልዩ ሃይል መካከል ከማውራ 15 ኪሜ ርቃ በምትገኘዋ ሮቢት አካባቢ እንዲሁም በላይ አርማጭሆ ዋና ከተማ ትክል ድንጋይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶአል። እስከትናንት ድረስ በአርሰዶ አደሩና በልዩ ሃይል መካከል በተደረገ የተኩስ ለውጥጥ ከ100 በላይ የልዩ ሃይል አባላት ሲገደሉ፣ ከ36 ያላነሱ ንጹሃን ዜጎች ደግሞ በልዩ ሃይል አባላት ተገድለዋል። ዛሬ በበርካታ መኪኖች የተጫኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የልዩ ሃይል አባላት ከባድ መሳሪያዎችን ሳይቀር ወደ ትክል ድንጋይ በማስገባቱ ህዝቡ ቤቶቹን ዘግቶ ከመቀመጡም በላይ፣ ትምህርት ቤቶች የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች በሙሉ ተዘግተዋል። የልዩ ሃይል አባላት የተገደሉባቸውን ባልደረቦቻቸውን ሊበቀሉ ነው በሚል የቻለው ወደ ጫካ መውጣቱንም ያካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
በርካታ የተገዱ የልዩ ሃይል አባላት በአዘዞ የመከላከያ ካምፕ እና በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የልዩ ሃይል አባላት እህትማማች ሴቶችን በጩቤ ገድለው መገኘታቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አስነዋሪ በሆነ መልኩ ባለትዳር ሴቶችን ሳይቀር መድፈራቸው የህዝቡን ቁጣ አባብሶታል በማለት ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ጥያቄውን ከሚያስተባብሩ ወገኖች መካከል አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰው ለኢሳት እንደተናገሩት በህዝቡ በኩል ከልዩ ሃይል አባላት መካከል 102 ከህዝቡ ደግሞ 33 ሰዎች ተገድለዋል ይላሉ።