ሐምሌ ፰ ( ስምንት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ በሳንጃ፣ በዳባት ፣ በደባርቅ እና በሌሎችም አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በአምባጊዮርጊስ ከተማ ዛሬ ጠዋት ህዝባዊ አመጽ የተቀሰቀሰ ሲሆን፣ ወታደሮች ሃይል ተጠቅመው ለማፈን ሞክረዋል። ይሁን እንጅ ውጥረቱ አሁንም ቀጥሎአል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ በጎንደር ከተማ እና በአካባቢው የተሰማራ ቢሆንም ወጣቶቹ ግን ያነሳነው የመብት ጥያቄ ካልተመለሰ ትግሉን እንቀጥላለን ይላሉ።
በሌላ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ህዝቡ ባለበት አካባቢ እንዲነሳ ጥሪ እያቀረቡ ነው። በባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆነች አስተያየት ሰጪ ኢሳትን በሚፈለገው መጠን አልቀሰቀሰም በሚል አስተያየቱዋን ጀምራ የባህርዳር ወጣት ዳር ሆኖ እየተጠባበቀ ነው ብላለች ።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ የኦሮሞና የጎንደር ህዝብ ደሙን እያፈሰሰ የሌላው አካባቢ ህዝብ ምን ይሰራል ሲሉ ጠይቀው፣ ለነጻነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ይነሳ ሲሉ ጥሪ ያቀርባሉ ።
ገዢው ሃይል በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የወልቃይት ጠገዴ የኮሚቴ አባላትን እንዲፈታ እና የተነሱትን ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመልስ ይህ ካልሆነ ግን ትግሉ ይቀጥላል ሲሉ የኮሚቴው አባላት እያስጠነቀቁ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ዴሞከራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄን በጠብ መንጃ አፈሙዝ ማቆም አይቻልም ሲል ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቋል።
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፋ የፖለቲካ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ውስጥ ትገኛለች ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ለሁሉም የሕዝብ ጥያቄ ምላሹ የኃይል እርምጃ የሆነው አገዛዙ መግደል፣ ማፈናቀል፣ ማሰደድ እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭቶችን መቀስቀስ ዋና ተግባሩ አድርጐታል ብሎአል።
በጐንደር ከተማ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተነሳው ተቃውሞ እንዲሁም በአዲስ አበባ ን/ስ/ላፍቶ ሀና ማሪያም ቀርሳ ኮንቶማ አከባቢ የተፈጠረው ግጭት አገዛዙ የፈጠረው ጭቆናና አፈና ውጤት ነው የሚለው ፓርቲው፣ የሕዝቡን ጥያቄ “የሌላ ኃይል ፍላጐት አስፈፃሚዎች ያነሳሱት ነው” በማለት መግለፁ ለሕዝብ ያለውን ንቀት የሚያሳይ ሆኖ አግኝተነዋል ሲል አክሏል።
“አገዛዙ በንፁሃን ዜጐች ላይ የወሰደውን ኃላፊነት የጐደለው እርምጃ እያወገዝን የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩነቱን ወደ ጐን በመተው ለዚህ ምስቅልቅል ምክንያት የሆነውን አፋኝ ስርዓት ለማስወገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጦ እንዲነሳ ጥሪ አቅርቧል።”