መስከረም ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአካባቢው የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው መስከረም 17 ቀን፣ 2008 ዓም አንድ የመከላከያ አባል የአሽሬ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ሁለት ወንድማማቾችን በጥይት የመታቸው ሲሆን አንደኛው ወጣት ተማሪ ወዲያውኑ ሲሞት ሌላው ደግሞ ቆስሎ ሆስፒታል ገብቷል።
ወታደሩ በወጣቶች ላይ የወሰደው እርምጃ ያበሳጨው ሌላ ወታደር ፣ ገዳዩን ወታደር ገድሎ እና አንዲት ሴት ወታደር አቁስሎ መጥፋቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ወታደሩን ለመያዝ ሙከራ ቢደረግም እስካሁን አልተሳካም። ከፍተኛ የተኩስ ለውውጥ መካሄዱን የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ህዝቡም በድርጊቱ በመበሳጨት ቁጣውን ሲገልጽ ውሎአል።
በአርማጭሆ አንዳንድ የገዢው ፓርቲ ታማኝ ወታደሮች በህዝቡ ላይ የሚፈጽሙትን ግድያ በመቃወም ፣ ባልደረቦቻቸው የአጸፋ እርምጃ ሲወስዱ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት የስማዳ ተወላጅ የነበረው መቶ አለቃ ደጀን ሞቅያለው ፣ በስሩ ያሉ ወታደሮች በህዝብ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ከህወሃት ወታደራዊ አመራሮች ቢታዘዝም፣ “ አላደርገውም” በማለቱ በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ህይወቱ ሲያልፍ፣ በህወሃት ደህንነቶች በኩልም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በዚሁ አካባቢ አገዛዙን እየተዉ የሚጠፉ ወታደሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየተበራከተ በመምጣት ላይ ነው። በሰሜን ጎንደር ህዝባዊ አመጽ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች አገዛዙን አናገለግልም በማለት ጠፍተዋል። በባህርዳርም እንዲሁ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ 5 የአማራ ልዩ ሃይል አባላት እስከ ጦር መሳሪያቸው ጠፍተዋል።
በርካታ ወታደሮች አገዛዙን ለኑሮ ብለው እንደሚያገለግሉ የሚናገሩት ምንጮች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገዛዙን መዳከም እያዩ በመጥፋት ላይ መሆናቸው ሰርዓቱ ተደጋጋሚ የቅጥር ማስታወቂያዎችን ለማውጣት ተገዷል።
በሌላ በኩል የአማራ ክልል ህዝብ የብአዴን ንብረት በሆነው ዳሸን ቢራ ላይ የጣለው ማእቀብ ውጤት እያመጣ መሆኑ ታውቋል። የድርጅቱን ምርት የሚገዙ ሰዎች ቁጥር ማሽቆልቆሉ፣ ድርጅቱን ለኪሳራ እንደሚዳርገው ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ድርጅቱ ሰራተኞች ይገልጻሉ።
ዳሸን ቢራ በአገዛዙ የተከፋውን የጎንደርን ህዝብ ልብ ለማለሳለስ ዛሬ ለተማሪዎች ደብተር በነጻ ሲያድል ውሎአል።