በሰሜን ጎንደር ህወሃት/ኢህአዴግ ለነጻነት የሚታገሉ አርበኞች ቤቶችን አፈረሰ

ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2009)

በሰሜን ጎንደር ቋራ በረሃ ለነጻነት የሚታገሉ አርበኞች ላይ ያነጣጠረ የቤት ማፍረስ ዘመቻ በአገዛዙ ሃይሎች መጀመሩን የኢሳት ምንጮች ገለጹ ። በቋራ ጉላን ከተማ ብቻ 200 ቤቶች ፈርሰዋል ።

ለነጻነት የሚታገሉ ሃይሎች መሬታቸው እንዳይታረስ ሲያደርግ የቆየው የአገዛዙ ወታደራዊ እዝ እርሻቸው ለስርአቱ ደጋፊዎች ሲሰጥ መቆየቱም ተነግሯል ።

የቋራ ወረዳ ኮማንድ ፖስት ወይም ወታደራዊ እዝ በኮለኔል ገብረመስቀል በየነ የሚመራ ሲሆን፣ ኮለኔሉ በምህረት ስም የአካባቢውን ህዝብ ትጥቅ ለማስፈታት ሞክሮ ባለመሳካቱ ህዝብ የማመስና ቤት የማፍረስ ዘመቻውን መቀጠሉ ተነግሯል። በተለይም ከቋራ ገበሬ ተነጥቆ ለሱዳን በተሰጠው መሬት ያሉ የባእድ ዜጎችን በመጠቀም የነጻነት ተፋላሚዎችን ለመያዝ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ታውቋል።

በህውሃት / ኢህአዴግ / የሚመራው አገዛዝ የህዝቡን የነጻነት ትግል ለማፈን የተለያዩ ዘዴዎችን ሲጠቀም መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ከወታደራዊ ግድያና አፈና በተጨማሪ የነጻነት ሃይሎች ቤተሰቦችን ማስጨነቅና ንብረቶቻቸውን መዝረፍ ሌላው የአፈናው አቅጣጫ መሆኑ ይነገራል። ለነጻነት በረሃ የገቡ ቤተሰቦችን ቤቶች ማቃጠል ከብቶቻቸውን መዝረፍ መሬታቸውን ነጥቆ መስጠትም ሌላው የማስፈራሪያ ዘዴ ነበር ። የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከሰሞኑ ብቻ በቋራ ወረዳ  ገላጉ ከተማ የነጻነት አርበኞች ቤቶችን ማፍረስ ጀምረዋል ። ቤተሰቦቻቸውን ያለመጠለያ በማስቀረቱም አካባቢያቸውን ለቀው ስደት ጀምረዋል ተብሏል። በከተማዋ እስከሁን ከ 200 በላይ ቤቶች  ሲፈርሱ መጠለያቸውን ያጡትም በምሬት ጫካ መግባታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።