ኀዳር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአፋር አጎራባች በሆኑ 15 ቀበሌዎች የድረቁ ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ ከ500 በላይ የቁም እንስሳት መሞታቸውን የሐብሩ ወረዳ የግብርና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡
ዝናቡ ለአንድ ወር በመዘግየቱ በሃምሌ ወር መጨረሻ መዝነቡ የሰብሉን እድገት ማስተጓጎሉን የሚናገሩት ባለሙያ፣ በወረዳው ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው የከብት መኖ እጥረት ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች አሁንም ችግሩ ተባብሶ በመቀጠሉ በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ስጋት ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡
ባለሙያው አክለውም አሁን ባለው ድርቅ ሁኔታ 500 የቁም ከብቶች መሞታቸውን ቢናገሩም ነዋሪዎች ከዚህ በላይ እየሞተባቸው እንደሆነ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡በተለይ በአሁኑ ወቅት ድርቁ ጉዳት እያደረሰ ያለው በጥጃዎችና ክበድ ላሞች ላይ የማስወረድና የሞት አደጋ በየጊዜው መከሰቱን ተናግረው፤ ይህን ተከትሎ የሚከሰቱ ተዛማች በሽታዎችም ለቁም እንስሳቱ ሞት መፋጠን በምክንያትነት እንደሚቆጠሩ ገልጸዋል፡፡
የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ስራው የሚሰራው በደጋውና ወይና ደጋው አካባቢ መሆኑን የገለጹት ባለሙያ፣ በቆላው አካባቢ የደን ሽፋን መመናመን መታየቱን ገልጸዋል፡፡ አካባቢው በከብት እርባታ የሚተዳደር ህብረተሰብ የሚኖርበት አካባቢ በመሆኑ የተፈጥሮ ሐብት ስራውን ለማከናዎንና አካባቢውን በደን ለመሸፈን አለመቻሉን ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
በአካባቢው ለድረቅ የተጋለጡ የቁም ከብቶች ከመቶ ሽህ በላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ባለሙያ ለእነዚህ ከብቶች ከመንግስት የቀረበው ደርቆሽ ሁለት ሽህ ኪሎ ግራም ብቻ በመሆኑ በቂ ቀለብ አልቀረበም፡፡ድርቆሹ በጣም ለተጎዱት ብቻ ለመስጠት መገደዳቸውን ሚናገሩት ባለሙያ ድርቁ በቀጣይ እንስሳቱን ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
አርብቶ አደሮች በዚህ ዓመት ሰብል ቢያጡ በቀጣዩ ዓመት ሊያመርቱ እንደሚችሉ የሚናገሩት ባለሙያ አንድ ከብት ቢሞትባቸው ግን በአንድ አመት መተካት ስለማይችሉ ህብረተሰቡ እንስሶችን ለማዳን በራሱ ጊዜ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከመንግስት የመጣው ድጋፍ ዝቅተኛ በመሆኑ ለአካባቢው ህብረተሰብ አሁንም ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ባለሙያው በአንክሮ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የንብ አናቢዎች ዙሪያ የሚሰሩት የወረዳው ባለሙያዎች ከአሁን በፊት በርካታ ማህበራት በስፋት ሲያንቀሳቀሱት የነበረው የዘመናው ቀፎ እንቅስቃሴ በድርቁ ምክንያት ንቦችን ለመቀለብ እንደተቸገሩ ይናገራሉ፡፡
በምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል በተከሰተው ድርቅ በርካታ እንስሳትና ሰዎች እየሞቱ ቢሆንም የገዢው መንግስት ጉዳዩን በአደባባይ በማመን ከህብረተሰቡና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ዕረዳታ አሰባስቦ ተጎጂዎችን በመርዳት ፋንታ ጉዳት አልደረሰም በማለት በየምክንያቱ ድግስ በመደገስ ገንዘብ ማባከኑ እንዳሳዘናቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡
ገዢው መንግስት ለኢህዲን-ብአዴን በዓል ካወጣው 300 ሚለዮን ብር በተጨማሪ ጋምቤላ ላይ ለሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በመቶ ሚሊዮኖች ብር ለማውጣት ሽርጉድ አያለ መሆኑ አስደናቂ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።