የካቲት ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እንደ ኢሳት ምንጮች መረጃ የሳንቃ ሁለተኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ መምህራን ፣የሀራ ሁለተኛ ደረጃ መምህራን፣የአንፈሁም የስሪንቃ ሁለተኛ ደረጀሰ መምህራን እና የጉባላፍቶ ወረዳ የገጠር መምህራን ስራ አቁመው ውለዋል። በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሳይማሩ ተመልሰዋል። በተለይ የሳንቃ መንህራን በፖሊስ ተከበው ከግቢው እንዳይወጡ ማስፈራራት ቢደረግባቸውም፤ አንድም መምህር ገብቶ ሊያስተምር አልቻለም።
በተመሣሳይ በደቡብ ጎንደር ዞን የአዲስ ዘመን እስቴ መካነ እየሱስ እና አንበሳሜ ሁለተኛ ደረጃ መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደርገዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ አፈረዋናት ትምህርት ቤት በትናንትናው እለት የስራ ማቆም ካደረጉት መምህራን ውስጥ 12ቱ በዛሬው እለት በኮማንድ ፖስት ተይዘው ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል።
ከእነዚህም መምህራን ውስጥ ገድፍ አለሙ: አለምፀሃይ አያሌው : እስከዳር እንግደው ፡ ዘልቃወርቅ ደሴ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡መምህራኑ በምን ምክንያት ነው የምንፈለገው? ብለው ሲጠይቁ ሰኞ እለት ባማስተማራችሁ፣እንዲሁም ማክሰኞ ለተደረገው የስራ ማቆም አድማ አነሳሽና ጠንሳሾች በመሆናችሁ ነው ተብለዋል፡፡ እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም ዞን በጃቢ ጠህናን ወረዳ በርካታ ት/ቤቶች እየተዘጉ እና መምህራንም እየታሰሩ መሆናቸውም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመምህራንን የስራ ማቆም አድማ ትከትሎ የኢሃዴግ አገዛዝ ለሰራተኞች ደሞዝ አልጨመርኩም ብሏል።
በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች ፣ ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ሲጨምር ለመምህራን ሳይደረግ ቀርቷል። ይህም አገዛዙ ለመምህራን ያለውን ንቀት ያሳያል በሚል መምህራን የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የኢሃዴግ አገዛዝ፣ ለሰራተኞች የደሞዝ ማስተካከያ እንጅ ጭማሪ አላደረኩም በማለት ቀደም ብሎ የሰጠውን መግለጫ ቀይሮታል። ፓርቲው ያወጣው ይህ መግለጫ ቀደም ብሎ ፓርላማው ካጸደቀው የደሞዝ ጭማሪ መግለጫ ጋር የሚጋጭ ነው።ፓርላማው ጥር ላይ ባካሄደው ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ በአገር ዓቀፍ ደረጃ የመንግስትሠራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የደመወዝ ጭማሪ እንዳጸደቀ ተናግሮ ነበር።
የደመወዝ ጭማሪው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ላይ ለመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ መንግስት በወሰነው መሰረት የተከናወነ መሆኑንም የመንግስቱ ሚዲያ ፓርላማውን ጠቅሶ ዘገበው ነበር፡፡
ይሁንና መንግስት አሁን ከመምህራን የተናሰበትን ተቃውሞ ለማብረድ የደሞዝ ማስተካከያ እንጅ ጭማሪ አላደረኩም ብሏል።