መጋቢት ፲፩ (አሥራ አንድ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አርበኞች ግንቦት7 ሰሞኑን በተከታታይ ካደረጋቸው ጥቃቶች መካከል አንዱ የሆነ ጥቃት በደንቢያ ከተማ ባለፈው ቅዳሜ ለሁለተኛ ጊዜ ተፈጽሟል። የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ጥቃቱን ተከትሎ ከተማዋ እንደገና በወታደሮች የተወረረች ሲሆን፣ በርካታ ሰዎች ጥቃት ፈጻሚዎችን አጋልጡ እየተባሉ ክፉኛ ተደብድበዋል። በጯሂት ከተማ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎም እንዲሁ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሟል።
በደንቢያ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመው ጥቃት በወረዳው ፋይናንስ ቢሮ አካባቢ ሲሆን፣ በአካባቢው የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ስብሰባ በማድረግ ላይ ነበሩ። በዚህ ጥቃት ምን ያክል ሰዎች እንደተጎዱ ወይም በጥቃቱ ስለደረሰው የንብረት ጉዳት የታወቀ ነገር የለም። የአይን እማኞች እንደሚሉት ግን ጥቃቱ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት አላደረሰም። በገዢው ፓርቲ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ በመፍጠሩ፣ ወታደሮች እርስ በርስ ሲወዛገቡ መታየታቸውን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በማክሰኚት አካባቢ ዳንጉላ ጭንጫዩ በሚባል ቀበሌ ላይ የአርበኞች ግንቦት7 ታጣቂዎችን ለማደን የሄዱ የገዢው ፓርቲ ወታደሮች ያልጠበቁት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የድርጅቱ አመራሮች ተናግረዋል። አበበ ታከለ የተባለውን የታጣቂዎች መሪን ጨምሮ 3 ታጣቂዎች መቁሰላቸውንም ድርጅቱ በላከው ሪፖርት ገልጿል።
በዚሁ አካባቢ የአርበኞች ግንቦት7 አባላት የሚፈጽሙት ጥቃት እየጨመረ መምጣት የአገዛዙ ወታደሮች ሃይላቸውን ወደ ሰሜን እንደገና እንዲስቡ እያደረጋቸው ነው።
በሌላ በኩል ቅዳሜ ማለዳ የደሴ ከተማ ዋናውን ወይን ቤት ሰብረው ከፍተኛ ቀጥር ያለው ታራሚ ያመለጠ ሲሆን፣ ታራሚዎችን ለማስቆም በተተኮሰ ጥይት የሶስት እስረኞ ህይዎት ሲያልፍ ፤ አራት እስረኞች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ይገኛሉ፡፡ አስራ አንድ እስረኞች በጠባቂዎች ላይ ጥቃት ፈፅመው እስር ቤቱን ሰብረው ማምለጣቸውን የወይን ቤቱ አዛዥ ኮማንደር ፅሀይ ተናግረዋል፡፡፡
ሌሎች ወገኖች በበኩላቸው ጥቃቱ የተቀነባባረና በመካሄድ ላይ ያለውን ትግል ተከትሎ የተፈጸመ ነው።