ጥር ፳፪(ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በአማራ እና በትግራይ አዋሳኝ ቦታዎች ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ የሚታየው ውጥረት እንደቀጠለ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ የአካባቢውን ህዝብ ለአመጽ ያነሳሳሉ ያላቸውን ሰዎች ለመያዝ መመኮሩ ብዙ ወጣቶች ቀያቸውን እየተዉ እንዲሸፍቱ አስገድዷቸዋል።
የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የአካባቢውን ወጣት እየሰበሰቡ የግንቦት7ትን መመሪያ እያስፈጸማችሁ ነው በማለት እያስፈራሩዋቸው ሲሆን ፣ ነዋሪዎቹ ግን ጥር 16 ባወጡት ያቁዋም መግለጫ ችግሩ በአስቸኳይ የማይፈታ ከሆነ አመጻቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ጥር 22 ደግሞ ብርሃኑ ጀግኔ የተባለ ፋርማሲስት ህዝቡን አስተባብረሃል በሚል በአብርሃ ጅራ ከተማ ተይዞ ቢታሰርም ህዝቡ በአንድነት በሰልፍ በመውጣት እንዲፈታ አድርጓል። የስልክ ኔት ወርክ በአካባቢው ተቋርጦ ከቆየ በሁዋላ ከትናንት ጀምሮ መመለሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።