በሰሜን ተራሮች የሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎችን ከፓርኩ ለማስወጣት የተጀመረው ዘመቻ ውዝግብ ቀሰቀሰ

ኢሳት (ሚያዚያ 2 ፥ 2009)

በህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ነዋሪዎችን ከፓርኩ ለማስወጣት የጀመረው ዘመቻ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ አለመግባባት ቀሰቀሰ።

በዚሁ ብሄራዊ ፓርክ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች በፓርኩ ውስጥ ለሚገኙ ብርቅዬ የዱር አራዊት ቁጥር መመናመን ምክንያት ሆነዋል በሚል አገዛዝ ከሶስት አመት በፊት ነዋሪዎችን የማስወጣት ሂደት መጀመሩ ይታወሳል።

በመጀመሪያ ዙር ከተካሄደው በዚሁ ዘመቻ ከ3ሺ አካባቢ ነዋሪዎች መካከል 418 የቤተሰብ አባላት ወደሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪ ነዋሪዎችን ለማስወጣት በቅርቡ እንቅስቃሴ መጀመሩን አሶሼይትድ ፕሬስ ሰኞ ዘግቧል።

ይሁንና በፓርኩ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች መንግስት ያቀረበላቸውን የካሳ ክፍያ አንቀበልም በማለት ፓርኩን ለቀው እንዳማይወጡ መግለጻቸውን የዜና አውታሩ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ረፖርት አመልክቷል።

በፓርኩ ውስጥ ለረጅም አመታት እንደኖሩ የሚናገሩት ነዋሪዎች መንግስት በካሳነት ያቀረበላቸው ስጦታ በቂ አለመሆኑን ይገልጻሉ። በመጀመሪያ ዙር ከፓርኩ እንዲሰፍሩ የተደረጉት ነዋሪዎች በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የፓርኩ ተወካይ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ ለአሶሼይትድ ፕሬስ ሲያሳውቁም ነዋሪዎቹ ግን የተሰጣቸው ካሳ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።

የዜና ወኪሉ ለፓርኩ ነዋሪዎች እየተካሄደ ያለን ስፍራ ለመመልከት ጥያቄን ቢያቀርብም ፈቃድ እንደተከለከለ በዘገባው አስፍሯል።

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በ38 መንደሮች ወደ 3ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎች ለረጅም ጊዜ የኖሩ ሲሆን፣ መንግስት ነዋሪዎቹን ሙሉ ለሙሉ ከፓርኩ ለማስወጣት እቅድ መንደፉ ታውቋል።

ይሁንና ለዱር አራዊት ቁጥር መመናመን ምክንያት ሆነዋል የተባሉት ነዋሪዎች መንግስት ወደ አዲስ ቦታ እንዲስፍሩ ያቀረበላቸው የካሳ ክፍያ በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል።

በቅርቡ በመንግስትና በነዋሪዎቹ መካከል የተደረገ ውይይትና ድርድርም በነዋሪዎቹ እምቢተኝነት መፍትሄ ሳይገኝ መቅረቱን አሶሼይትድ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።

በዚሁ ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘዞ አዱኛ ውይይቱ ወደ ፊት በመግባባት ሊፈታ ይችላል ሲሉ ለዜና አውታሩ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ነዋሪዎቹን ለማስፈር ምን ያህል ካሳ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነ የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ነዋሪዎች እያቀረቡት ያለው ጥያቄም በዘገባው አልተጠቀሰም።

በተለያዩ አካባቢዎች መንግስት ከልማት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከመኖሪያ ቀያቸው የሚያነሷቸው ነዋሪዎች በቂ ካሳ አልተሰጠንም በማለት ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ከፓርኩ ይዞታ ሁለት ሶስተኛው እጅ የሚሆነው በፓርኩ ውስጥ በሚኖሩ ገበሬዎች ነዋሪዎች ለግጦሽ፣ ለግብርናና ለመኖሪያነት ውሎ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።