በርካታ የጎንደር እስር ቤቶች በእስረኞች ተጨናንቀዋል ተባለ

ጥቅምት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ኮማንድ ፖስት እያለ ራሱን የሚጠራው የህወሃት/ኢህአዴግ የአፈና መስመር ዛሬ በጎንደርና ባህርዳር እንዲሁም በዙሪያ ከተሞች ከፍተኛ አፈሳ ሲያካሄድ ውሎአል። በጎንደር ቀበሌ 2፣ 4 እንዲሁም 14 በርካታ ሰዎች ኢሳትን ታያላችሁ በሚል መታሰራቸውን ተከትሎ እስር ቤት በእሰረኞች ተጨናንቀው ታይተዋል።ፖሊሶች ጣራ ለጣራ እየወጡ ዲሽ ሲነቅሉ መዋላቸውም ታውቋል።

በዳባትም እንዲሁ በርካታ ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል። በባህርዳር ከተማ ትናንት የተጀመረው አፈሳና ዲሽ የማስነቀል እርምጃ ዛሬም ተጠንክሮ ቀጥሎአል።

ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓም ከፌደራል ፖሊሶች ጋር በመዋጋት አንድ ፖሊስ ገድለውና አንድ ፖሊስ አቁሰለው የተገደሉት የጢስ አባይ የጎበዝ አለቃ የነበሩትን የአቶ ምክሩ ብርሃኑን ዘመዶች እና ሌሎችንም ወጣቶች ለመያዝ የፌደራል ፖሊስ ወደ አካባቢው በብዛት በመሄድ ዛሬም ችግር ሲፈጥሩ የዋሉ ሲሆን፣ 34 ወጣቶች ተይዘው ወደ ባህርዳር ተወስደዋል። በርካታ እናቶችም ልጆቻችሁን አምጡ ተብለው መታሰራቸው ታውቋል።

የአቶ ምክሩ አጎት እጅ አልሰጥም በማለት ጫካ የወጡ ሲሆን፣ ሌሎች ወንድሞቻቸውና ወጣቶችም ጫካ ገብተዋል። ሌሎች ዘመዶቻቸው ደም ይመልሳሉ በሚል እየታሰሩ መሆኑንም የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።