የካቲት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሶማሊ ክልል በቀላፎ አካባቢ የሚኖሩ 19 የየረር ባሬ ጎሳ የአገር ሽማግሌዎች በክልሉ ውስጥ የተፈጸመውን ከፍተኛ እልቂት ለጠ/ሚንስትሩ አቤት ለማለት ወደ አዲስ አበባ በሄዱበት ወቅት አካባቢውን በሚጠብቁ ልዩ ሃይሎች ተይዘው መታሰራቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከእስር ያመለጡ አንዳንድ ሽማግሌዎች በትናንትናው እለት ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ከዚህ ቀደም በልዩ ሚሊሺው በቀጥታ የተገደሉትን የ47 ሰዎች ስም ፣ ከቆሰሉ በሁዋላ በህክምና እጦት የሞቱትን የ 17 ሰዎች ስም እንዲሁም ከ100 በላይ ቁስለኞችን እና የታሰሩትን ሰዎች ስም ዝርዝር የያዘውን ደብዳቤ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፣ በአሁኑ አጠራር ለሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ፣ በመንግስት እንደሚደገፍ ለሚነገርለት ለኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለእንባ ጠባቂ እና በድጋሜ ለጠ/ሚንስትር ጽ/በት አስገብተዋል። በደብደቤያቸው ላይ ለጠ/ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ያስገቡትን ደብዳቤ ቁጥር በመጥቀስ ፣ ጠ/ሚንስትሩ እስካሁን መልስ እንዳልሰጡዋቸው በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸዋል።
የአገር ሽምግሌዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሀመድ ኡመር እና ጄኔራል አብርሀም በቅጽል ስማቸው ኳታር የሚመራው ልዩ ሚሊሺያ እየተባለ የሚጠራው ሀይል ታህሳስ 1 እና 2 በከፈተው ተኩስ በትምህርት ላይ የነበሩ ህጻናትንና ወጣቶችን ጨምሮ 47 ሰዎችን መግደሉን የሟቾቹን ስም ዝርዝር በመጥቀስ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወቃል።
ልዩ ሚሊሺያው ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንዳሉ ተኩስ መክፈቱን የአገር ሽማግሌዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራሉ መንግስት በአስቸኳይ ደርሶ እንዲታደጋቸውም ጠይቀዋል።
የየረር ባሬ ጎሳ አባላት የክልሉ መንግስት እንደ ተወላጅ ባለመቁጠር ጭቆና እንደሚያደረስባቸው በመግለጽ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ መንግስት ልዩ ሚሊሺያዎችና በየረር ባሬ ጎሳ አባላት መካከል ተደጋጋሚ ግጭት ሲደረግ ከቆየ በሁዋላ ሰሞኑን መሳሪያ ለማስፈታት ወደ አካባቢው የተጓዘው የክልሉ ልዩ ሚሊሺያ ሃይል ካፍ እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት ላይ በከፈተው ተኩስ ህጻናትንና ሴቶችን ጨምሮ 47 ሰዎች መገደላቸውን ፣ ጥር 11 በተቀሰቀሰው ግጭት ደግሞ ከ100 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንና 17 ሰዎች በህክምና እጦት መሞታቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የብሄረሰቡ ተወካይ ለኢሳት ገልጸው ነበር።
ዜናው በኢሳት መተላለፉን ተከትሎ የሚሊሺያ ሃይሉ በሶስተኛው ቀን 16 የአገር ሽማግሌዎችን ይዞ ማሰሩንም መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፉት 6 ቀናት የታሰሩትን የአገር ሽማግሌዎች ጨምሮ እስካሁን ከ35 በላይ የብሄረሰቡ ተወካዮች ታስረዋል።
የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነር ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም።