ጥር 16 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአዲስ አበባው ወኪላችን እንደገለጠው፣ በርካታ የኦሮሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በጄነራል ከማል የሚመራው ኦነግ፣ የመገንጠል አጀንዳን ሰርዞ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት አሳዛኝ ሁኔታ አላቆ፣ አገሪቱዋን ለመምራት የወሰደውን እርምጃ አድንቀዋል።
ለደህንነቱ ሲባል ስሙን መግለጽ ያልፈለገ አንድ የኦነግ ደጋፊ እንደገለጠው ፤ አለም ወደ አንድ እየተቀራረበች በመጣችበት ጊዜ እና በአሁኑ አለም ህልውናን ጠብቆ ለመኖር አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ባስፈለገበት ሁኔታ ፣ ድርጅቱ ይህን ተገንዝቦ የወሰደውን እርምጃ ከልብ ይደግፋል።
ተማሪው እንዳለው በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ኢፍትሀዊና ህገወጥ ድርጊቶች በኦሮሞ ህዝብ ላይ ተወስዷል። ይህንን መካድ ፈጽሞ አይቻልም; ይሁን እንጅ እኛ ወጣቶች ከታሪኩ ተምረን በአዲስ አስተሳሰብ ወደ ፊት መራመድ ካልቻልን በድሮ በሬ እያረስን ልንኖር አንችልም ብሎአል።
ኦነግ ድሮም ቢሆን የመገንጠልን አጀንዳ እንደ ትግል ስትራቴጂ እንጅ እንደግብ አለማስቀመጡን የሚጠቅሰው ተማሪው፣ ምናልባትም የጄኔራል ከማል ቡድን የወሰደው እርምጃ ድርጂቱን ወደ ፊት አንድ እርምጃ ሊወስደው ይችላል ሲል ተናግሯል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኦሮሞ ተወላጆች የጄነራል ከማል ኦነግ በወሰደው እርምጃ እየተወያዩ እና ድጋፋቸውን ለመግለጥ የሚችሉበትን መንገድ እየፈለጉ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የሶስተኛ አመት የህግ ተማሪ የሆነ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ነው።
ተማሪው የኦፌዴን ደጋፊ መሆኑን ቢገልጥም፣ ኦነግን እንደ ኦሮሞ ህዝብ ትክክለኛ ወኪል አድርጎ እንደሚቆጥረው ይናገራል። እኛ ኦሮሞዎች በፓርቲዎች ብዛት ብንከፋፈልም፣ የአሮሞን ችግር በተመለከተ ሁላችንም ተመሳሳይ አቋም አለን፣ የእስካሁኑ ልዩነታችን በችግሩ አፈታት ዙሪያ ነበር ሲል አብራርቷል።
ተማሪው እንደሚለው አንዳንድ የኦሮሞ ድርጅቶች የኦሮሞ ችግር የሚፈታው የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር በሰላማዊ መንገድ ሲፈታ ነው ብለው በማመን በሰላማዊ ትግል በህጋዊ ፓርቲ ስር ሆነው እየታገሉ ነው፣ ሌሎች ደግሞ የኦሮሞ ችግር የሚፈታው የኦሮሞ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብቱን መጠቀም ሲችል ነው ይላሉ። የጄኔራል ከማል ቡድን በአገር ውስጥ በሰላማዊ ትግል ከሚታገሉት ኦህዴድና ኦህኮ የሚለየው ትግሉን በሰላማዊ ትግል ለማካሄድ ፈቃደኛ አለመሆኑ ብቻ ነው በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
የኦሮሞ ተማሪዎች የመነጋገሪያ አጀንዳ የጄኔራል ከማል ቡድን የወሰደውን እርምጃ ጥቅምና ጉዳቱን መመዘን ሆኗል የሚለው ተማሪው፣ ብዙ ተማሪዎች ውሳኔውን በአወንታዊነት እንደተቀበሉት አክሎአል።
በጄኔራል ከማል የሚመራው ኦነግ የመገንጠል አጀንዳን በመተው የመለስ ዜናዊን መንግስት በመጣል ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት እንደሚታገል መግለጡ ይታወሳል።