በርካታ ኢትዮጵያውያን፦መለስ ሥልጣን በቃኝ ማለታቸውን ”የተለመደ ቧልትና ፌዝ”ሲሉ አጣጣሉት

ግንቦት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መለስ  እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2015 ማለትም የዛሬ ሦስት ዓመት ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ እና ከዚያ በሁዋላ በማናቸውም የመንግስት የሥልጣን ቦታ ላይ እንደማይቀመጡ መናገራቸውን በርካታ ኢትዮጵያውያን፦”የተለመደ ቧልትና ፌዝ”ሲሉ አጣጣሉት።

መለስ ይህን ያሉት ፤  ሰሞኑን ከሲሲቲቪ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ ለቢቢሲ እና ለሌሎች ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ጭምር ፦”የሚቀጥለው ተርም የመጨረሻዬ ነው” እያሉ ቃለ-ምልልስ እየሰጡ ለበርካታ ዓመታት ከወንበራቸው ሳይነሱ መቆየታቸውን ያስታወሱ በርካታ ኢትዮጵያውያን፦”አባባሉ፤ መለስ ውጥረትን ለማርገብ የሚጠቀሙበት ስትራቴጂ ይመስላል።በምርጫ 97 ወቅት ውጥረት ሲበዛባቸው ፦”ከእንግዲህ አንድ ተርም ነው የምቆየው አሉ።ሆኖም፤በ 2000 ምርጫ ሥልጣናቸውን አልለቀቁም” ብለዋል።

መለስ፤ከሁለት ዓመት በፊት  ከኢትዮጵያ ፈርስት ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስም፤ እንደደከማቸው እና ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ማረፍ እንደሚፈልጉ መናገራቸው ይታወሳል።

ይሁንና፤መለስ ቀደም ሰል ከሥልጣን ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ በተናገሩባቸው አጋጣሚዎች፤”ሆኖም ድርጅቴ ካልፈቀደልኝ በኔ ፍላጎት ብቻ መወሰን አልችልም” የምትል ቅጥያ ሲናገሩ የሚደመጡትም፤ “እኔ ስልጣን ለመልቀቅ ብፈልግም፤ድርጅቴ ከለከለኝ የሚል መቼት ለመሥራት ነው”ሲሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን የዜናው ቪዲዮ በተለጠፉባቸው ድረ-ገፆች ስር አስተያዬታቸውን አስፍረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ራሳቸው  ስልጣን መልቀቅ በተናገሩ ቁጥር ፦”መለስ በዓለማቀፉ ግንኙነታችን ላይ  ያስገኘልን ጥቅም በምንም የሚተካ አይደለም። እሱ ከሥልጣን የሚለቅ ከሆነ፤  እነዚህ ሁሉ ነገሮች ዝግ ይሆናሉ” በማለት በኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ ቅስቀሳ የሚያደርግ ቡድን በራሳቸው በመለስ ተላላኪዎች መቋቋሙ በስፋት ይነገራል።

ከዚህም ባሻገር  የ ኢህአዴግ ነባር አመራር፤ ቦታውን ለአዲስ ተተኪዎች ማስረከብ አለበት በሚል  መርህ፦ አዲሱ ለገሰን፤ተፈራ ዋልዋንና አቦይ ስብሀት ነጋን ጨምሮ በርካታ የ ኢህአዴግ አባላት  ከተቀመጡበት ከፍተኛ የስልጣን እርከን እንዲወርዱ ሲደረግ መለስም ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው እንደሚነሱ  በመስማማት ነበር።

ኢህአዴግ ሰባተኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በ አዋሳ ሲያካሂድ ከሥልጣን የተሻሩት የብአዴኑ አቶ ተፈራ ዋልዋ ፦”ከስልጣን በመውረድዎ ምን ተሰማዎት?” ተብለው በጋዜጠኞች ሲጠየቁ፦” ደስታ ነው የተሰማኝ። እኔ ብቻ ሳልሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ራሳቸው ሥልጣናቸውን በቅርቡ ለተተኪ አመራር ያስተላልፋሉ”ማለታቸው አይዘነጋም።

ይህ ሁሉ ከሆነ በሁዋላ ነው ፦”የትራንስፎርሜሽን እቅዱም ሆነ የህዳሴው ግድብ ያለ መለስ መሪነት አይሳካም” በሚል ሀሳብ የመለስ ከሥልጣን መልቀቅ ፈፅሞ የማይታሰብ እንደሆነ ውስጥ ውስጡን ሲነገር የሰነበተው።

በመሆኑም እነ ተፈራና እነ አዲሱ ከሁለት ዓመት በፊት “መተካካት” በተሰኘው ዘዴ ከስልጣናቸው ሲነሱ መለስም በቀጣዩ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ሥልጣን እንደሚለቁ ታሳቢ የተደረገ ቢሆንም፤ አቶ መለስ ግን ሥልጣን የሚለቁት በ2015 እንደሆነ ነው ለሲሲቲቪ ቴሌቪዥን የነገሩት።

አቶ መለስ እንዳሉት እስከ 2015 በሥልጣን የሚቆዩ ከሆነ፤ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት በመቀመጥ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ከመንግስቱ ሀይለማርያም በሰባት ዓመት ብልጫ ይኖራቸዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide