በርካታ ኢትዮጵያውያንን በህገወጥ መንገድ በማዘዋወር የተጠረጠረው ሃዱሽ ኪዳኑ በቁጥጥር ስር ዋለ

ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2016)

በርካታ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ዜጎችን በህገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር ወንጀል የተጠረጠረና ለዘጠኝ አመታት ያህል ሲፈለግ የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ በስዊዘርላንድ በቁጥጥር ስር ዋለ።

ሃዱሽ ኪዳኑ የተባለው ይኸው የ58 አመት ኢትዮጵያዊ በማልታ መንግስት የሚፈለግ በመሆኑ የስዊዘርላንድ መንግስት ተጠርጣሪውን ለማልታ መንግስት አሳልፎ መስጠቱም ታውቋል።

ሃዱሽ በማልታ በነበረበት ወቅት በህገ-ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ክስ ተመስርቶበት እንደነበርና የዋስትና መብት ተሰጥቶት የፍርድ ቤት ውሳኔን ይጠበቅ እንደነበር የማልታ ፖሊስ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቋል።

ይሁንና፣ ግለሰቡ ከዘጠኝ አመት በፊት የተሰጠውን የዋስትና መብት በመጠቀም፣ ህገወጥ በሆነ የጉዞ ሰነድ ከሃገሪቱ መኮብለሉን ኢንዲፐንደት የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

ለዘጠን አመት ያህል ጊዜ ዱካው ጠፍቶ የነበረው ይኸው ኢትዮጵያዊ በስዊዘርላንድ መንግስት በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለማልታ መንግስት መሰጠቱ ታውቋል።

የማልታ አቃቢ ህግ በበኩሉ ሃዱሽ ኪዳኑ ከዚህ በፊት ተሰጥቶት የነበረው የዋስትና መብት ተነስቶ ተመስርቶበት የነበረው ክስ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የተሰጠውን የዋስትና መብት በመጣሱ ምክንያት የአንድ ወር የእስር ቅጣት የተላለፈበት ተከሳሹ በርካታ ሰዎችን በማልታ በኩል ወደ ጣሊያንና የአውሮፓ ሃገራት በህገ-ወጥ መንገድ አጓጉዟል የሚሉ ክሶች እንደሚጠብቁትም ለመረዳት ተችሏል።

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር በዋለ ጊዜ የተገኘበት ከ11 ሺ ዩሮ በላይ ገንዘብም እንዲወረስ የማልታ ፍ/ቤት መወሰኑን ኢንዲፐንደንት ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።

ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ብቻ እንደሚኖርባት የሚነገርላት ማልታ በማዕከላዊ የሜዲትራኒያን ባህር ላይ የምትገኝ ደሴት ስትሆን፣ ከሰሜን የአፍሪካ ቀጠና ለጣሊያን የወደብ ከተማ ለሆናችው ሲሲሊ ቅርብ መሆኗ ይታወቃል።

ይህችን ታሪካዊ ደሴት በመጠቀም በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመጓዝ እንደመሸጋገሪያ እንደሚጠቀሙባት የማልታው ኢንዲፐንደንት ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።