ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት በሃገር ውስጥ ጥጥን ለማምረት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችንና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን ቢመድብም አብዛኛው የጥጥ ልማት ሳይለማ መቅረቱ ተገለጠ።
ለዚሁ የእርሻ ዘርፍ ወደ 3 ቢሊዮን ብር አካባቢ በብድር መልክ ቢሰጥም አብዛኛው ገንዘብ ለተባለው አላማ እንዳልዋለ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ይፋ ማድረጉ ታውቋል።
ለባለሃብቶች ከተሰጠው ብድር ውስጥም ባለሃብቶቹ ምን ያህሉን ለጥጥ ልማት እንዳዋሉትና የተቀረውንም ገንዘብ የት እንደገባ ለማወቅ አንድ ብሄራዊ ቡድን ተቋቁሞ ጉዳዩን መመርመር እንደጀመረ የጨርቃ ጨርቅና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት መግለፁን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ ከ100ሺ በላይ ለጥጥ ልማት ቢሰጥም አብዛኛው መሬት ልማት እንዳልተካሄደበትም ታውቋል።
በጥጥ እርሻ ላይ የተፈጠረው ችግር ከታወቀ በኋላም ኢንስቲትዩቱ ህጋዊ እርምጃን እንደሚወስድ የመንግስት ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከውጭ ባለሃብቶች በሰጠው ሰፋፊ የእርሻ መሬት ላይ ተደራራቢ ብድር ተሰጥቶ በመገኘቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የገባበት አለመታወቁን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ መንግስት ለባለሃብቶች ሲሰጥ የነበረውን ሰፋፊ የእርሻ መሬት ፕሮግራም ያቋረጠ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ለዘርፉ የሚሰጠውን ብድር አስቀርቷል።
በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ከባንኩ የተበደሩት ገንዘብ ሳይመልሱ ከሃገር መውጣታቸውንም የመንግስት ባለስልጣናት ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በጥጥ ልማት ላይ ደርሷል የተባለን ኪሳራ ለማጣራትም በብሄራዊ ደረጃ የተቋቋመ ቡድን በክልሎች ጉብኝት እያደረገ መሆኑ ታውቋል።
ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ቢወስዱም ወደስራ የገቡት ከ40 በመቶ እንደማይበልጡ የኢንስቲትዩቱ የጥጥ ልማት ዳይሬክተር አቶ ባንቴ ካሳ ለመገናኛ ብዙህኛ ገልጸዋል።
በሃገር ውስጥ ይመረታል ተብሎ የተጠበቀው የጥጥ ምርት ባለመመረቱም ምክንያትም የአልባሳት ፋብሪካዎች የጥጥ ምርት እጥረት አጋጥሟቸው የሚገኝ ሲሆን፣ መንግስት የጥጥ ምርትን ከውጭ ለማስገባት እቅድ መያዙንም ለመረዳት ተችሏል።