ሐምሌ ፳፩ ( ሀያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች ዘጠኝ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ለቀናት ያካሄዱትን የረሃብ አድማ ተከትሎ ራሳቸውን የሳቱ ሲሆን፣ ወደ ሆስፒታል ሳይወሰዱም የእስር ቤቱ የህክምና ክፍል በእያንዳንዳቸው እጅ ላይ ፈሳሽ ምግብ ( ግሉኮስ) እንደተከለላቸው ታውቋል።
የአቶ ደጀኔ ጣፋ ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ አሰለፈች ሙላቱ እንደገለጹት፣ እስረኞቹ ለሳምንት ያክል ምግብ ባለመብላታቸው ራሳቸውን መሳታቸውንና ወደ ሆስፒታል ሳይወሰዱ ግሉኮስ እንደተተከለላቸው ተናግረዋል። እስረኞችን ለአመጽ ያነሳሳሉ በሚል ጨለማ ቤት ውስጥ የተወረወሩት እስረኞች፣ የአያያዛቸው ሁኔታ እንዲለወጥ በተደጋጋሚ አቤት ሲሉ ቆይተዋል።
የረሃብ አድማውን ያደረጉት አቶ በቀለ ገርባ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ ፍቅረማርያም አስማማው፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ማስረሻ ታፈረ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላ ፣ ዮናታን ተስፋዬ እና ጉርሜሳ አያና ናቸው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የእሰረኞች ቤተሰቦች መረጃ ለመገናኛ ብዙሃን ትሰጣላችሁ በሚል ችግር እየደረሰባቸው ነው።