መስከረም ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኤልኒኖ የአየር መዛባት ምክንያት በተፈጠረው ድርቅ ሳቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕፃናትን ጨምሮ ከ4.5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከፍተኛ በሆነ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆኑንና አፋጣኝ የሆነ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአውስትራሊያው ቻይልድ ፈንድ በሪፖርቱ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ያለው የርሃብ ሁኔታ እጅግ አስጊ መሆኑንና በተለይ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብና በሶማሌ ክልሎች ለአስከፊ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ድርጅቱ አትቷል፡፡
ቻይልድ ፈንድ አገልግሎት እየሰጠባቸው ባሉ አካባቢዎች እስከ 211 ሺህ ሰዎች ከዚህ ውስጥ ደግሞ 74 ሺህ የሚሆኑት ህጻናት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፍልጋቸው ገልጿል። ለሶስት ወራት የምግብ ድጋፍ ለማድረግ ቢያንስ 3.5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልገውም አስታውቋል።
ለሁለት ተከታታት የዝናብ ወቅቶች ወቅቱን ጠብቆ ዝናብ ባለመጣሉ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ አርሶአደሮችና አርብቶአደሮች ለችግር መጋለጣቸውንና የችግሩ ዋናው ገፈት ቀማሾች ደግሞ ሕፃናት መሆናቸውንና አፋጣኝ የሆነ እርዳታ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ካልቀረበ ችግሩ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችልም ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።