የካቲት ፳፰ ( ሃያ ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተመድ የሰባዊ ድጋፍ አስተባባሪ እንዳስታወቀው 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በረሃብ ቢጠቁም፣ ምግብ፣ ወሃና መድሃኒት ለማቅረብ አልተቻለም። አለማቀፉ ማህበረሰብ፣ ህዝቡን ለመደገፍ የሚያስፈልገውን 900 ሚሊዮን ዶላር በፍጥነት ካለገስ፣ ከፍተኛ ሰባዊ ቀውስ ይከሰታል ሲል አስጠንቅቋል። በየቀኑ በርካታ ዜጎች እየተጎዱ መሆኑን የጠቀሰው ተመድ፣ በተለይ ልጆችን በፍጥነት መታደግ ካልተቻለ በሁዋላ ላይ ጉዳቱን ለመቀነስ ከባድ ይሆናል ብሎአል።
የበልግ ዝናብ ይቀነሳል የሚለ ፍርሃት መኖሩ የተረጂዎቸን ቁጥር እንደሚጨምረው ተመድ አስጠንቅቋል። በሌላ ዜና ድግሞ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት መጨመሩን ማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከዓመት እስከ ዓመት የዋጋ ንረት በከፋ ሁኔታ ተባብሶ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በወርሃዊ ጥናታዊ ሪፖርቱ አመላክቷል። አጠቃላይ የዋጋ ንረቱ ከአምናው ጋር ሲተያይ 6.8 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
የ12 ወራት አማካኝ የምግብ የዋጋ ንረት ከነበረበት 5.9 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ደግሞ 7.8 በመቶ የዋጋ ንረት ጭማሪ ታይቶባቸዋል። የምግብ ዋጋ ካለፈው ዓመት የካቲት ወር ጋር ሲነጻፀር 7.8 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች በበኩላቸው የ6.2 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል።
በአገር አቀፍ የችርቻሮ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 7% በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የምግብ እና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች 7.8 ከመቶ፣ ልብስና መጫሚያ በ3.8 ከመቶ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት መስሪያ እቃዎች፣ ውሃ እና ኢነርጂ በ9.1 ከመቶ፣ ቤት ማስጌጫዎች የቤት ቁሳቁስ እና የቤት ሰራተኛ ደመወዝ በ4.9 በመቶ፣ ሕክምና 11.2 ከመቶ፣ ትራንስፖርት 7.0 ከመቶ፣ መገናኛ በ2.1 ጫማሪ ታይቶባቸዋል።
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመላው ኢትዮጵያ የምግብ ዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ ጫማሪ ታይቶበታል። ዳቦና እህል በ3.8 ከመቶ፣ ሥጋ በ9.5 ከመቶ፣ ወተት አይብና እንቁላል በ7.4 ከመቶ፣ ዘይትና ቅባቶች በ7.3 ከመቶ፣ ፍራፍሬ በ3.8 ከመቶ፣ አትክልት፣ ጥራጥሬ፣ ድንችና ሌሎች ስራስሮች በ10.3 ከመቶ፣ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን የኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ዝርዝር ጥናታዊ ሪፖርት ያሳያል።