በረሃብ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በሜሪላንድ ሲልቨር ስፕሪንግ ተካሄደ 

ኢሳት (ሚያዚያ 10 ፥ 2008)

በግሎባል አልያንስ፣ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ እንዲሁም በዲሲ ግብረ ሃይል አማካኝነት በጋራ የተዘጋጀውና በኢትዮጵያ ውስጥ በረሃብ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ።

እሁድ ሚያዚያ 9 ቀን 2008 ዓም በሜሪላንድ ከተማ በሚገኘው ሸራተን ሆቴል የተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም “ወገን መታደግ ቀን” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን በግዛቱ እና በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ የተጀመረው በሃይማኖት አባቶች መልዕክትና ስለሃገራችን ፀሎት በማድረግ ሲሆን፣ በማስከተልም ግሎባል አሊያንስ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን  የሰራቸውን ዋና ዋና ስራዎች በቪዲዮ የተደገፈ ሪፖርት አቅርቧል። የግሎባል አሊያንስ ሰብሳቢ አርቲስት እና አክቲቪስት ታማን በየነ ለተሰብሳቢው ንግግር አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ በየአመቱ የሚያከናውነውን “ ኢሳት የእኔ ነው” የቀጥታ ስርጭት ለዚህ ፕሮግራም መታሰቢያ በማድረግ ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚገኙ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን በረሃቡ አደጋ ዙሪያ መልዕክት እንዲያስተላልፉ ተደርጓል። በእለቱ አስተያየታቸውን ለኢሳት የሰጡ ኢትዮጵያውያን የረሃቡን አደጋ በጋራ መረባብረብና ለወገናችን በመድረስ ታሪካዊ ሃላፊነታችንን መወጣት እንደሚገባን አስታውቀዋል።

በሲልቨር ስፕሪንግ ሸራተን ሆቴል በተዘጋጀው “ወገን መታደግ ቀን” የተለያዩ ፕሮግራሞች የቀረቡ ሲሆን፣ ከተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ35ሺህ ዶላር በላይ መገኘቱን አዘጋጅ ኮሚቴው አስታውቋል።

በተለይም የካሳንቺስ አካባቢ ልጆች በጋራ በመሆን 5ሺህ ዶላር በማዋጣት አስተዋጽኦ አድርገዋል።