(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 4/2010)በሞያሌ የተፈጸመውን ጭፍጭፋ በስህተት ነው በሚል በኮማንድ ፖስቱ የተሰጠውን መግለጫ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ።
በሞያሌ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል ሲልም ጠንካራ አቋም ይዟል።
በክልሉ ፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ እንደተናገሩት የተፈጸመው ግድያ በስህተት እንዳልሆነ መረጃ አለ።
ድርጊቱን የፈጸሙት ብቻ ሳይሆኑ የመከላከያና የኮማንድ ፖስቱ አዛዦች ጭምር በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል አቶ ታዬ ደንደአ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንዲህ ዓይነት አቋም ሲይዝ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም።
ከዚህ ቀደምም ከህወሀት አገዛዝ ጋር ፍጥጫ ውስጥ በመግባት የክልሉን መንግስት አቋም በአደባባይ ያስታወቀባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቄሮውች ላይ ምርመራ መጀመሩን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሀሰት መሆኑን በመግለጽ ምርመራ ካስፈለገም የፌደራል ፖሊስ ምን አገባው የሚል አቋም መያዙ የሚታወስ ነው።
ሰሞኑን በሞያሌ የተከሰተውን ዕልቂት በተመለከተ የኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት የሰጡትን ምላሽ እንደተለመደው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ውድቅ አድርጎታል።
የሴክተሪያቱ ተወካይ ሌ/ጄ ሀሰን ኢብራሂም ከ10 በላይ ሰዎች በግፍ ለተጨፈጨፉበት ድርጊት በሰጡት መግለጫ ጉዳዩ በስህተት የተከሰተ ነው።
ርምጃም እንወስዳለን ማለታቸው ከፍተኛ ቁጣን አስከትሏል።
የአገዛዙን መግለጫ በይፋ በመቃወምም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አቋሙን ገልጿል።
በክልሉ መንግስት የፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ በሰጡት ቃለመጠይቅ በስህተት ነው ተብሎ የተሰጠው መግለጫ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ የሞያሌው ጭፍጨፋ ሆን ተብሎ ለመፈጸሙ መረጃዎች እንዳሏቸውም ይገልጻሉ።
የተፈጸመው በስህተት አለመሆኑን እናምናለን ያሉት ሃላፊው ስህተት ነው ማለቱ ህዝብን መስደብ ነው ሲሉም ይናገራሉ።
አንዳንዶቹ ተንበርከኩ ተብለው ግድያ እንድተፈጸመባቸው አቶ ታዬ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ገልጸዋል።
ለሞያሌው ጭፍጨፋ ተጠያቂዎቹ ድርጊቱን የፈጸሙት ብቻ እንዳልሆኑም አቶ ታዬ ጠቅሰዋል።
ትዕዛዝ ያስተላለፉት የኮማንድ ፖስት ሃላፊዎችና የመከላከያ አዛዦችም በህግ ሊጠየቁ ይገባል በማለት ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን አቋም በተመለከተ የኮማንድ ፖስቱ ምላሽ አልሰጠም። በሞያሌ ዛሬም ነዋሪው በሽሽት ላይ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።
በተለይም ከአጎራባች ቀበሌዎች የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ለማወቅ ተችሏል።
በቅዳሜው ጭፍጨፋ በአጋዚ ወታደሮች 13 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።