በሞያሌ ውጥረት መንገሱ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 10/2010)በሞያሌ በቦምብ ጥቃት 3 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ተነገረ።

በሞያሌ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያና የሶማሌ ድንበር አዋሳኝ ጫካዎች ሕዝቡ መሳሪያ እየያዘ መግባቱን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች እንቅስቃሴ በመከላከያና በፌደራል ፖሊስ አባላት የመገደብ ስር መጀመሩንም ለማወቅ ተችሏል።

በሞያሌ ዙሪያ ባሉ ቀበሌዎች ህዝቡ እየተጠራራ እርስ በርሱ ሲመካከርና ለበቀል መሳሪያ ሲሰበሰብ እንደዋለና ከሞያሌ በ40 እና 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ ድንበሮች መጓጓዙ ተሰምቷል።

በአካባቢው ያንዣበበው የግጭት ሁኔታም እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው መረጃዎች ያመለክቱት።

የአካባቢው ነዋሪዎች የአፀፉ ርምጃ ለመውሰድ በሞያሌ ዙሪያ ባሉ የሶማሌ እና የኦሮሚያ ድንበር ጫካዎች መሳሪያ እየያዙ መግባታቸውም ተሰምቷል።

በሞያሌ ከተማ የህዝብ እንቅስቃሴ በአጋዚ እና የፌደራል ፖሊስ ጥምር ጦር ተገድቧል።

ህዝቡ ከቤቱ እንዳይወጣም በአጋዚ አፈሙዝ ታግቷል ነው የተባለው።

በሞያሌ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ትናንት ከሰዓት በኋላ  በጥይት ተመቶ ከጥቅም ውጭ በመሆኑ ከተማዋ በጨለማ ተወራ አድራለች።

የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ እስካሁንም እንደተቋረጠ መሆኑም ታውቋል።

ትራንስፈርመሩ በጥይት መመታቱን ተከትሎ 2 የሶማሌ ገሪ ጎሳ አባላት በአንድ መከላከያ መገደላቸው ታውቋል።

ትላንት በመናኸሪያ ላይ በተጣለው 2 የእጅ ቦምብ 3 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ በነበረው ተኩስ ከቆሰሉት መካከል ክፉኛ የተጎዱት ወደ ያቤሎ  ሆስፒታል ሪፈር ተብለው ሄደዋል።