(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 10/2011) በሞያሌ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ እንደአዲስ ባገረሸው ግጭት ከ80ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ።
በግጭቱ የተፈናቀሉት አብዛኞቹነዋሪዎች በአቅራቢያ ባሉ ወረዳዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ነው ለማወቅ የተቻለው።
አንደኛ ሳምንቱን የደፈነው ግጭት ከትላንት ጀምሮ ጋብ ያለ ቢመስልም የተኩስ ድምጽ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች እንዳለ ተገልጿል።
በሞያሌ ከህክምና መስጪያ ማዕከላት ውጪ የከተማዋ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መቆሙንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የቦረና ዞን የመንግስት ሃላፊዎች ለዶቼቬሌ እንደገለጹት ለቀናት በዘለቀው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉት ዜጎች ድሬ፣ሜጋ፣ ሚዮ እና ሠርባ በተባሉት የሞያሌ አጎራባች ከተሞች እና ወረዳዎች በጊዜያዊነት ተጠለልው ይገኛሉ።
ዛሬ ሞያሌ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባት እንደሆነ የገለጹት የኢሳት ምንጮች በማንኛውም ሰዓት ግጭቱ ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት አብዛኛው ነዋሪ ከተማዋን ለቆ መውጣቱን ጠቅሰዋል።
ሞያሌ ከተማ ላይ የተፋጠጡት የቦረናና ገሪ ማህበረሰቦች ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ሰላም እንዲመጡ በፌደራል መንግስት በኩል ጥሪ የተደረገ ሲሆን የመከላከያ ሰራዊት ወደ አከባቢው በመግባት ላይ መሆኑ ታውቋል።
ከትላንት በስቲያ በከተማዋ በሚገኝ በቀለ ሞላ ሆቴል በተፈጸመ ጥቃት የመንግስት ሃይሎችን ጨምሮ 12 ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።