(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 9/2010) በሞያሌ ከተማ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት 3 ሰዎች ተገደሉ።
ከ50 በላይ ሰዎችም ቆስለዋል።
በአውቶብስ መናሃሪያ አካባቢ በተፈጸመው በዚሁ የቦምብ ጥቃት ከፍተኛ ደም የፈሰሳቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታል ባለመወሰዳቸው ህይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት በሞያሌ ዳግም ባገረሸው የሶማሌና የኦሮሞ ተወላጆች ግጭት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን የዛሬው የቦምብ ጥቃት ዳግም ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር እንደሚያያዝ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች ጥቃቱ የቦምብ ብቻ እንዳልሆነ የሚያሳዩ ናቸው።
በሆስፒታል ቆስለው ህክምና ላይ የሚገኙ ሰዎችን የተመለከቱ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከቆሰሉት መሀል በጥይት የተመቱም አሉ።ከቦምቡ ጥቃት በተጨማሪ የተኩስ እሩምታ ይሰማ እንደነበረም የአይን እማኞች ገልጸዋል።
በሞያሌ የአውቶብስ መናሃሪያ አካባቢ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት የአራት ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱንም ዘግይተው በሆስፒታል አካባቢ የሚገኙ ምንጮች ካሰራጩት መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ለኢሳት በውስጥ መስመር ከሞያሌ በተላከው መረጃ ላይ የተገደሉት የ4ሰዎች ስም ዝርዝር ተገልጿል።
ከድሮ ገለቱ ኑሩ፣ ጀማል አህመድ፣ ምርጫ ሼህ አብዱራህማንና ገዛኒ ሶሬሳ በዛሬው ጥቃት የተገደሉ መሆናቸው ተገልጿል።
የቆሰሉት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ሆስፒታል ገብተው ህክምና ላይ ያሉት 60 መድረሳቸውም ታውቋል።
ለኢሳት በፎቶግራፍ ጭምር ታግዘው የደረሱት መረጃዎች ከቆሰሉት መካከል አብዛኞቹ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ደም የሚፈሳቸው ሰዎች በቶሎ ህክምና ባለማግኘታቸው ህይወታቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ የተመለከተው።
የሟቾቹ ቁጥር ከተጠቀሰው ሊበልጥ እንደሚችል የሆስፒታል ምንጮች ገልጸዋል።
በፍንዳታው ወቅት የተኩስ ድምፆች እንደነበሩ የሚጠቅሱት ምንጮች በጥይት ተመተው በሆስፒታል የሚገኙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።
በህክምና ማዕከላት ከነበረው ህዝብ ውጭ በአብዛኛው እንቅስቃሴ በልዩ ሃይል እና በህወሃት የአጋዚ ጦር ቁጥጥር ስር እንደሚገኝም ታውቋል። መንገዶች ተዘግተዋል። የከተማዎ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ቆሟል።
ባለፈው ሳምንት በሶማሌ ገሪ ጎሳና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል ያገረሸው ግጭት ከዛሬው ፍንዳታ ጋር ስለመያያዙ የታወቀ ነገር ባይኖርም ግጭቱን ተከትሎ የተፈጸመ መሆኑ ይነገራል።
ሳምንት በዘለቀው ግጭት በህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን መዘገባችን ይታወሳል። የዛሬውን ጥቃት በተመለከተ ሃላፊነት የወሰደ አካልም የለም።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ ቢሮ የቦምብ ጥቃቱን የፈጸመው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል መሆኑን ገልጿል።
የአካባቢው ባለስልጣናትም የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልን ወታደራዊ ዩኒፎርም በለበሱ ታጣቂዎች ጥቃቱ የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ተጠያቂ አድርገዋል።
የሶማሌ ክልል መንግስት ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት የሰጠው ምላሽም ሆነ ማብራሪያ የለም።
ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ በህወሀት የአጋዚ ወታደሮች በሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች ላይ በተወሰደ ርምጃ በትንሹ 13 ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለው ኬንያ መግባታቸው የሚታወስ ነው።