በሞያሌ በቦረና ኦሮሞዎችና በገሪ ሶማሊዎች መካከል የተጀመረው እርቅ መጨናገፉ ተሰማ

በሞያሌ በቦረና ኦሮሞዎችና በገሪ ሶማሊዎች መካከል የተጀመረው እርቅ መጨናገፉ ተሰማ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ/ም ) ነሐሴ 15 2010 ዓ. ም የከተማዋ ሙስሊሞች የአረፋ በዓልን ለማክበር ለስግደት የወጡበትን አጋጣቢ በመጠቀም፣ አንድ አባት ባደረጉት ጥረት የቦረና እና ገሪ ህዝብ እርስ በርስ እንዲገናኙና እርቀ ሰላም እንዲያወርዱ ለማድረግ መቻላቸውን ተከትሎ፣ በድርጊቱ የተደሰተው የከተማው ህዝብ በአዋጅ የተጠራ ይመስል አደባባይ በመውጣት እየተቃቀፈ ሲላቀስ፤ ደስታውን ሲገልጽ እና ይቅር ሲባባል ውሎ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህ መልካም ድርጊት ያለኛ እውቅና የተካሄደ ነው፣ ለአመታት ደም የተፋሰሰበት ጉዳይ በዚህ መንገድ አይጠናቀቅም ያሉት የከተማዋ ቄሮዎች፣ በወሰዱት እርምጃ የከተማው ሰላም እንደገና እንዲታወክና ውጥረቱ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን ነዋሪዎች በሃዘኔታ ገልጸዋል። በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል የተጀመረው ግንኙነት እንደገና የተቋረጠ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ በከተማዋ ወጣት ቄሮዎች ድርጊት በእጅጉ ማዘናቸውንና የክልሉ መንግስት ጣልቃ ገብቶ የተጀመረው የእርቅ ሂደት የሚቀጥልበትን መፍትሄ እንዲፈልጉ ተማጽነዋል።
በአሁኑ ሰዓት ግጭት የሌለ ቢሆንም፣ በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት ግን እንደተቋረጠ ነው።