ኢሳት (ታህሳስ 14 ፥ 2009)
ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ላይ ነበሩ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ሲጓዙበት የነበረ ተሽከርካሪ የመጋጨት አደጋ አጋጥሞት በትንሹ ሰባት መሞታቸውን የሞዛምቢክ ባለስልጣናት አርብ አስታወቁ።
ከአደጋው የተረፉ 34 ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ እየደረሰባቸው ካለ እንግለት ለመታደግ ሲባል የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ስደተኞቹ ሃሙስ ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓጓዙ ማድረጉ ታውቋል።
ኢትዮጵያውያን ስተደኞቹ አምስት ወር የፈጀ ጉዞን አድርገው ሞዛምቢክ ከደረሱ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በመጓዝ ላይ እንዳሉ የተሽከርካሪ አደጋ ደርሶ ሰባቱ ስደተኞች ህይወታቸው ማለፉን የስደተኞች ድርጅት አመልክቷል።
ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች የተወሰኑ አደጋ በደረሰበት ስፍራ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ ፔምባ ተብሎ በሚጠራ ሆስፒታል ለህክምና ከተወሰዱ በኋላ ህይወታቸው ሊያልፍ መቻሉን መረዳት ተችሏል።
ከዚሁ አደጋ የተረፉት 34 ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለስደተኞች ማቆያ የሚሆን ቦታ በመጥፋቱ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ባለ አንድ መጠለያ ተይዘው እንዲቆዩ መደረጉን የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ገልጿል።
ይሁንና ስደተኞቹ እንዲቆዩ የተደረገበት ቦታ ለኢትዮጵያውያኑ ምቹ ባለመሆኑ እንዲሁም ለችግሩ በመጋለጣቸው ምክንያት ስደተኞቹ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ተመልክቷል።
ይሁንና በትራፊክ አደጋው ህይወታቸው ያለፈው ኢትዮጵያውያን አስክሬናቸው ወደ ሃገር ቤት ይወሰድ አይወሰድ የታወቀ ነገር የለም።
በሞዛምቢክ የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ለኢትዮጵያውያኑ የምግብ፣ አልባሳትና የተለያዩ ድጋፎች እንዲያገኙ ያደረጉ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሞዛምቢክ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል።
በማላዊ፣ ታንዛኒያ፣ እና ናሚቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገሪቱ ገብታችኋል ተብለው በእስር ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይ ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ተለያዩ ሃገራት በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።