ጥር 3 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአማራ ክልል በምእራብ ጎጃም ዞን በይልማና ዴንሳ ወረዳ በአዴት ከተማ በተነሳ የህዝብ ተቃውሞ አንድ ባለስልጣን ሲገደል ሌሎች ሁለት ፖሊሶች እና ሌላ አንድ ባለስልጣን ከፉኛ ቆስለዋል።
ማምሻውን በደረሰን ዜና ደግሞ በጽኑ ከቆሰሉት መካከል አንደኛው ህይወቱ አልፎአል።
በትናንትናው እለት የወረዳው ባለስልጣናት የጨረቃ ቤቶችን ለማፍረስ በተንቀሳቀሱበት ጊዜ፣ ህዝቡ ቤታችንን አታፈርሱም በማለት ከባለስልጣኖች ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር።
ችግሩን ለመፍታት ባለመቻሉም ህዝቡ በባለስልጣናቱ ላይ ድንጋይ መወርወር መጀመሩን ፣ ትንሽ ቆይቶም ዱላ ያለው በዱላ፣ ሌላው ደግሞ በድንጋይ በፖሊሶች ላይ ጥቃት ፈጽሞአል።
ጸቡ እየተካረረ ሲመጣ፣ አንድ ነዋሪ ከፖሊሱ ጠመንጃ በመቀማት ግብረሀይሉን የመራውን የወረዳውን የኢንዱስትሪ ሀላፊ የሆነውን ይበሉ ደሴን ገድሎ፣ የከተማውን አፈ ጉባኤ አቶ እንድሪስን ደግሞ አቁስሎአል።
በተኩስ ልውውጡ መሀልም ሁለት ፖሊሶች ቆስለዋል። ፖሊሶች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃም በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ድርሷል። አብዛኞቹ ቁስለኞች በሞጣ ሆስፒታል ተወስደው እየታከሙ ሲሆን፣ የመንግስት ባለስልጣናቱ እና ፖሊሶች ደግሞ ወደ ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ተወስደዋል።
ሟቹ አቶ ይበሉ ደሴ በቅርቡ ከጎንች ቆለላ ቀበሌ ወደ አዴት ከተማ የተዛወረ ነበር። ከተወሰኑ ሰአታት በሁዋላ የፌደራል ፖሊስ አካባቢውን የተቆጣጠረ ሲሆን፣ ዜናውን እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ውጥረቱ እንዳለ ነው።
የፌደራል ፖሊሶች ታጣፊ ክላሽንኮቭ ቀምተው የወሰዱትን ግለሰቦች በማደን ላይ ነው። አዴት ወረዳ በምርጫ 97 ቅንጅትን መምረጡ ይታወሳል።