በምግብ አቅርቦት ላይ እስከ 27 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ተከሰተ

ኢሳት (ግንቦት 22 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች በመሰረታዊ የምግብ አቅርቦቶች ላይ እስከ 27 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን የአለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ሰኞ አስታወቀ።

በሃገሪቱ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ 10.2 ሚሊዮን ሰዎች የሚያስፈልገው የምግብ ድጋፍ በወቅቱ ባለመድረሱና የተረጂዎች ቁጥም እየጨመረ በመሄድ በምግብ ሸቀጣሸቀጦች ላይ ከመቼው ጊዜ በላይ የዋጋ ንረት መከሰቱ አሳሳቢ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።

አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በሃረሪ ኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የኑሮ ውድነት ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በመሰረታዊ የምግብ ግብዓቶች ላይ የተከሰተው የዋጋ ንረት እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል የአለም ምግብ ፕሮግራም በወቅታዊ የኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ ዙሪያ አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።

ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ ነዋሪዎች የምግብ ዋጋ መጨመርን ባሳየ ጊዜ እጅጉኑ ተጎጂ እንደሚሆኑና ድርቁ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እያስከተለ መቀጠሉን ድርጅቱ ገልጿል።

በመጋቢት ወር በነበረ የጥራጥሬዎች ዋጋ በሚያዚያ ወር 27 በመቶ እድገትን ያስመዘገበ ሲሆን፣ በተለይ በድርቅ በተጎዱ በስድስት ክልሎች የመሰረታዊ የምግብ ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው ጭማሪን እያሳየ መሆኑም ታውቋል።

መንግስት በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ስንዴና ዘይትን ከውጭ ሃገር ማስገባት ቢጀምርም፣ መዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች እጥረቱ አልባት አለማግኘቱን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

በተለይ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ የእርዳታ ለተጋለጡ ከ10 ሚሊዮ በላይ ሰዎች የሚያስፈልገው የምግብ ድጋፍ በተገቢው መጠን ባለመገኘቱ ሳቢያ ችግሩ እየተባባሰ በመቀጠል ላይ መሆኑን አለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት ይገልጻሉ።

ይህንንም ተከትሎ ለተረጂዎች የሚያስፈልገው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ወደ 1.5 ቢሊዮን  ማደጉን የአለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ለተረጂዎች ከሚያስፈልገው ገንዘብ መካከል ግማሽ ያህሉ ብቻ የተገኘ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት መኖሩን ይገልጻሉ።

ያጋጠመውን የዕርዳታ አቅርብት ተከትሎ ተረጂዎች በወር በሚያገኙት ፍጆታ ላይ ቅነሳ መደረጉንም ለመረዳት ተችሏል።