በምዕራብ ዕዝ በመከላከያ አባላት መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በርካታ ወታደሮች መቁሰላቸው ታወቀ
(ኢሳት ዜና የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ/ም) የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከ10 ቀናት በፊት በባህርዳር ውስጥ በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የምዕራብ ዕዝ ምድብ ውስጥ ወታደሮች ከብሄር ጋር በተያያዘ እርስ በርስ በመታኮሳቸው፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወታደሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በወቅቱ ሌሊቱን የተኩስ ድምጽ ሲሰሙ ያደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በሁኔታው ተደናግጠው ነበር። የክልሉ የኢሳት ወኪል ባደረገው ማጣራት እንዳረጋገጠው ፣ ግጭቱ የተነሳው ከብሄር ጋር በተያያዘ መሆኑንና ወታደሮቹ ጎራ ለይተው ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ በርካታ ወታደሮች ተጎድተዋል። ግጭቱ እንደበረደ በተለይ የአማራ እና የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ግጭት በመቀስቀስና በማቀጣጠል ሰበብ በወታደራዊ ካምፑ ውስጥ እንዲታሰሩ ተደርጎ ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጿል። ወታደሮቹ የታሰሩት በዚሁ መኮድ እየተባለ በሚጠራው ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ነው።
በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ተመሳሳይ የሆኑ ግጭቶች ሲነሱ የመጀመሪያ አለመሆኑንና በተለይ በምዕራብ እዝ ወታደራዊ ካምፕ የወታደሮች የእርስ በርስ ግጭት እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተስፋ የቆረጡ የፌደራል ፖሊስ አባላት ስራቸውን በፍጥነት እየለቀቁ ነው። በመላ አገሪቱ የሚታየው ሁኔታ እንዲሁም በየጊዜው ከህዝብ ጋር የሚያደርጉት ግጭት፣ የስነ ልቦና ጫና እየፈጠረባቸው አጋጣሚውን እየተጠቀሙ ስራቸውን በብዛት እየለቀቁ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።