በምዕራብ አርሲ በሚገኙ ከተሞች የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ወደ ግጭት ተለወጠ

ኢሳት (ሃምሌ 18 ፥ 2008)

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ለወራት በክልሉ ከቆየው ተቃውሞ ጋር ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲለቀቁ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ወደ ግጭት መለወጡን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።

በዶዶላ፣ አዳባ፣ አሳሳ፣ እና አካባቢው ከሰኞ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለውን ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ለማዋል የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተኩስ ዕርምጃን እየወሰዱ እንደሚገኝ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች በክልሉ ለወራት ከቆየውን ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱና በክልሉ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ይሁንና፣ በየከተሞቹ የተቀሰቀውሰውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር ከሻሸመኔ ከተማና ሌሎች ስፍራዎች በተሽከርካሪ በርካታ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ወደስፍራው ማቅናታቸውንና እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በምዕራብ አርሲ ዞን እየተካሄደ ያለውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎም ወደተለያዩ አጎራባች ስፍራዎች የሚወስዱ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን፣ ድርጊቱ በነዋሪው ዘንድ ውጥረት ማንገሱን እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።

ሰኞ እስከ ሰዓት በኋላ ድረስ የተኩስ ድምፅ ሲሰማ መዋሉን የተናገሩት ነዋሪዎች ግጭቱ እልባት ባለማግኘቱ ምክንያት በነዋሪዎች ላይ የደረሰን ጉዳት በአግባቡ ማወቅ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በዶዶላና አዳባ ከተሞች በርካታ የጸጥታ ሃይሎች በመስፈር ላይ እንደሚገኙ ለኢሳት ያስታወቁት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በዞኑ የሚገኙ ነዋሪዎች መንገዶችን በመዝጋት በክልሉ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ጥሪን እያቀረቡ መሆኑን አክለው አስረድተዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት በክልሉ ለወራት የዘለቀውን ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ውሏል ቢሉም አሁንም ድረስ በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞዎች ዳግም በማገርሸት ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በክልሉ በመካሄድ ላይ ስላለው ተቃውሞ በቅርቡ ሪፖርቱን ያወጣው ሂሁማን ራይትስ ዎች ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ግድያ እንደተፈጸመባቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለእስር መዳረጋቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ተቃውሞው ዳግም በመካሄድ ላይ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።