በምዕራብና በምስራቅ ጉጂ ዞኖች የሚካሄደው ተቃውሞ ቀጥሎአል

በምዕራብና በምስራቅ ጉጂ ዞኖች የሚካሄደው ተቃውሞ ቀጥሎአል
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ/ም) ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሻኪሶ አካባቢ የሚካሄደው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ ተቃውሞውን ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በአጋዚ ወታደሮች ተደብድበው ሆስፒታል መግባታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። ድብደባ ተፈጽሞባቸው ሆስፒታል ከተኙት መካከል 6 የኮሌጅ መምህራንም ይገኙበታል።
የተቃውሞው መነሻ የሼክ ሙሃመድ አላሙዲን ኩባንያ የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ለተጨማሪ 10 አመታት የወርቅ ማውጣት ስራ እንዲሰራ የፈቃድ እድሳት ማግኘቱ ነው። በአዶላና ሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ ወርቅ የማውጣት ስራ የሚሰሩ ኩባንያዎች የሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች በአካባቢው ህዝብ ላይ የጤና ችግር እየፈጠሩ መምጣታቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሚድሮክ ላለፉት 20 አመታት ወርቅ እያወጣ በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ቢያገኝም ለአካባቢው ህዝብ የሰራው ስራ አለመኖሩ ለተቃውሞው መነሻ ሌላው ምክንያት ነው።
ትናንትና እና ዛሬ በርካታ የአጋዚ ወታደሮች ወደ አካባቢው በመግባታቸው ውጥረቱ መጨመሩን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ በተለይ የኦሮምያ ክልል ስምምነቱ ሲፈረም እንደማያውቅ መግለጹ፣ ህዝቡን ይበልጥ እንዳስቆጣው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የአዶላ ወዮ መምህራን ኮሌጅ ውስጥ የሚያስተምሩ 6 መምህራንን ጨምሮ 17 ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ የእስረኞች ቁጥር እጅግ በርካታ መሆኑን ይናገራሉ።