ሰኔ ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ካለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ በደንበጫ የተጀመረው የተማሪዎች እና የመምህራን አድማ መቀጠሉን ተከትሎ ፣ፖሊሶች በሃይል በወሰዱት እርምጃ በርካታ ተማሪዎች ተጎድተዋል። ቁጥራቸው በውል ያልተወቀ የ11ኛ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ተይዘው መታሰራቸውን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ግጭቱ ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል ብለዋል::
መምህራን የጠየቅነው የደሞዝ ማስተካከያ ካልተደረገ የተማሪ ውጤት አንሰጥም ማለታቸውን ተከትሎ፣ ተማሪዎች ከመምህራን ጎን በመቆም ተቃውሞ ማሰማት ሲጀምሩ፣ ፖሊሶች ተማሪዎችን እየደበደቡ አስረዋል። ዛሬ ተማሪዎች እየተፈተሹ ወደ ትምህርት ቤት ከገቡ በሁዋላ እንደገና ተቃውሞአቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ መምህራንም መልቀቂያ ስጡን እንጅ አንሰራም በሚል አድማውን አጠናክረዋል። የወረዳው ባለስልጣናት ችግሩን በሃይል ለመፍታት ሙከራ ማድረጋቸው በአካባቢው ያለውን ውጥረት እንዳባባሰው ነዋሪዎች ገልጸዋል።