(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 9/2010) በምስራቅ ጎጃም መርጦ ለማርያም ብረት ጭኖ ወደ ትግራይ እያመራ የነበረ ከባድ ተሽከርካሪ በህዝብ ተቃውሞ መታገቱ ተሰማ።
ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ እንደተመለከተው ቁርጥራጭ ብረት የጫነው ተሽከርካሪ ወደ ትግራይ ክልል እያመራ መሆኑ ጥቆማ የደረሰው የመርጦ ለማሪያም ከተማ ነዋሪ ተሽከርካሪውን በማስቆም ተቃውሞውን ሲገልጽ ነበር።
በህዝቡና በአካባቢው ባለስልጣናት መሃል ውዝግብ መነሳቱም ተሰምቷል።
በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር ዞን ህዝቡን መሳሪያ ለማስፈታት በተንቀሳቀሱ የኮማንድ ፖስት ወታደሮችና የሚሊሺያ አባላት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በተወሰደው በዚሁ የማጥቃት እንቅስቃሴ መንገድ መሪውን ጨምሮ ሁለት የሚሊሺያ አባላት መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ምስራቅ ጎጃም መርጦ ለማርያም አሮጌ ድልድይ ነበራት።
አዲስ ድልድይ ተሰርቶላት አገልጎሎት ላይ መዋሉ በተገለጸ ሰሞን የተከሰተው ነገር ነው ህዝብን በቁጣ አደባባይ እንዲወጣ ያደረገው።
የአሮጌው ድልድይ ብረቶች ተነቃቅለው በሶስት ተሽከርካሪዎች ተጭነው ከከተማዋ ሊወጡ መሆኑ እንደተሰማ የመርጦ ለማርያም ነዋሪ ተጠራሮቶ ተሽከርካሪዎቹን ማገቱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የአሮጌው ድልድይ ብረቶች በገበያ ላይ የሌሉ በጥንካሬያውም ተመራጭ ናቸው።
ለነዋሪው የደረሰው መረጃ ብረቶቹን ጭነው ከከተማዋ ሊወጡ የተዘጋጁት ተሽከርካሪዎች መዳረሻቸው ትግራይ ክልል መሆኑን የሚገልጽ ነው።
ውስጥ ለውስጥ መረጃው ተዳርሶ ስለነበረ ተሽከርካሪዎቹ ከተማዋን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት በነዋሪው ታግተው እንዲቆሙ ተደርገዋል።
የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናትና ፖሊስ ተሽከርካሪዎቹን ሊያስለቅቋቸው ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም በነዋሪው ተቃውሞ ሊሳካ አልቻለም።
ኢሳት የተሽከርካሪዎቹ መዳረሻ ትግራይ ክልል ስለመሆኑ ማረጋገጫ ባያገኝም ነዋሪው የትም ይሁን የት የድልድዩ ብረቶች ከከተማው መውጣት የለባቸውም በሚል አቋም መጽናቱን ለማወቅ ተችሏል።
ተሽከርካሪውቹ በታገቱበት ቆመው የሚገኙ ሲሆን ሌሊቱን ተደብቀው እንዳይወጡ በሚል ነዋሪው በመነጋገር በከተማዋ መውጪያዎች የተደራጀ ሃይል ለማስቀመጥ እንዳቀደ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ጉዳዩን በተመለከተ ወደ መርጦ ለማርያም ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤትና ፖሊስ ስልክ በመደወል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር ትጥቅ ለማስፈታት በተንቀሳቀሰው የኮማንድ ፖስት ሃይል ላይ ጥቃት መሰንዘሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሚያዚያ 7 እና 8 ቀን 2010 በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ትጥቅ ለማስፈታት የተንቀሳቀሰው ይህው የኮማንድ ፖስት ሃይል በደረሰበት ድንገተኛ ጥቃት ሙትና ቁስለኛ መሆኑ ታውቋል።
ለኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች መንገድ በመምራትና በመጠቆም የተሰማራው አንድ የአካባቢው ሰውና ሁለት ወታደሮች በተፈጸማባቸው ጥቃት መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በተመሳሳይ ሰሜን ጎንደር ዞን በአዲአርቃይ ዛሪማ ፣ በሳንጃ ማርያም በተባሉ አካባቢዎችም የመሳሪ ማስፈታት ዘመቻ ላይ በነበሩ የኮማንድ ፖስት ወታደሮች ላይ ጥቃት መሰንዘሩንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከህዝቡ የሚደርስበትን ጥቃት ለመመከት ያልቻለው የህወሀት አገዛዝ ወታደሮቹን በፒካፕ እና በኦራል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ በማቆም በጭነት ተሽከርካሪዎችና አይሱዙ መኪናዎች የታጠቁን ወታደሮቹን እያስገባ መሆኑንም የአካባቢው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በዚህም ሙከራ ድንገተኛ የመሳሪያ ገፈፉ ለማድረግ የታቀደው ዘመቻም በህዝቡ ንቁ ርምጃ ሊከሽፍ መቻሉን ነው የደረሰን መረጃ ያመለከተው።
የህወሓት አገዛዝ በአማራ ክልል መሳሪያ ለመንጠቅ የሚያደርጋቸው ዘመቻዎች በአብዛኛው በህዝቡ የአጸፋ ጥቃት እየተመከቱ መሆናቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችን የሚታወስ ነው።