ሰኔ 9 ፥ 2009
በምስራቅ ኢትዮጵያ ሃርላ በሚባል አካባቢ በመሰማራት ቁፋሮ ሲያደርጉ የነበሩ የስነ ምድር ተመራማሪዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት በ10ኛው ክፍለ ዘመን የንግድ ማዕከል የነበረ አንድ ከተማ ማግኘታቸውን ገለጹ። ከግብጽ፣ ከህንድና፣ ከቻይና ወደ ከተማው የገቡ የተለያዩ ቁሳቁሶችም መገኘታቸው ተገልጿል። ከማዳጋስካር፣ ከማልዲቭስ እና ከየመን ጭምር የመጡ የተለያዩ ጌጣጌቶች በአካባቢው ተቀብረው መገኘታቸው ቢቢሲ በድረገጹ አስነብቧል።
ከዚህ በተጨማሪ የስነ-ምድር ተመራማሪዎች በ12ኛው ክ/ዘመን የተገነባ መስጊድ ማግኘታቸውንና፣ ይህም መስጊድ ከሶማሌና ታንዛኒያ ከሚገኙት መስጊዶች ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል። የስነምድር ተመራማሪዎች ቅሪቶቹ አፍሪካ የሚገኙ የሙስሊም ማህበረሰቦችን ቁርኝት አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮፈሰር ቲሞቲ ኢንሶል የተባሉ የኤክሴተር ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ እንደተናገሩት፣ “የተረሳ ከተማ” ተብሎ የተገለጸው ጥንታዊ ከተማ ከተለያዩ ክፍለ አለማት ለሚመጡ ነጋዴዎች የንግድ ማዕከል እንደነበረ አመላካች ነው ብለዋል።
በቦታው የ300 ሰዎች የተቀበረ ቅሪተ አካል መገኘቱን የገለጹት የምርምር ቡድኑ አባላት፣ ሰዎቹ በምን ምክንያት ሊሞቱ እንደቻሉ ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ሰዎቹ ሲመገቡ የነበሩት ምግብ ምን ይዘት እንደነበረውም ጭምር ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ ተናግረዋል።
በሚቀጥለው አመት ተጨማሪ ቁፋሮዎች በአካባቢው እንደሚካሄዱ ቡድኑ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጿል።