በምስራቅ ሸዋ ጨፌ ዶንሶ ተቃውሞው ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 30/2010)በምስራቅ ሸዋ ጨፌ ዶንሶ ተቃውሞው ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉ ታወቀ።

በርካታ የመንግስት ተቋማት በእሳት ቃጠሎ ወድመዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ህዝቡን ለማረጋጋት በመሞከር ላይ ናቸው። ሁኔዎች ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆኑ የሰጉ የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቶችን እያነጋገሩ መሆኑ ተገልጿል።

በምንጃር ሸንኮራ ዛሬ መንግስት የጠራው ስብሰባ በህዝብ ተቃውሞ መቋረጡን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል በመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ማድረጋቸው ታውቋል።

በዛሬው የጨፌ ዶንሳ ተቃውሞ በርካታ ተቋማት ወድመዋል። ፍርድቤቶች; የድርጅትና የመንግስት ጽ/ቤቶች፡ ማዘጋጃ ቤትና ሌሎች ተቋማት በህዝብ በተወሰደ ርምጃ በከፊልና ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በምስራቅ ሸዋ ጨፌ ዶንሳ ሶስተኛ ቀኑን በያዘው ተቃውሞ በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የመንግስት መስሪያ ቤቶች በቃጠሎ ወድመዋል።

እስከ 15 የሚደርሱ ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል። ከከተማዋ በ500 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሚሳኤል ምድብ እየተባለ የሚጠራው የአየር መቃወሚያን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች የተከማቹበት ቦታ፣ በልዩ ሁኔታ እየተጠበቀ ነው።

በትምህርት ቤቶችና የህዝብ ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት ሰርጎ ገቦች የህዝቡን ተቃውሞ ለማበላሸት ሆን ብለው ያደረጉት ነው ተብሏል።

ከአረርቲ 10 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የቻይና የቺፑድ ፋብሪካ በህዝብ ተቃውሞ መውደሙን የገለጸው የአማራ ክልል ቴሌቪዥን የህዝቡ ተቃውሞ የመብራት መቋረጥ ብቻ እንዳልሆነ ዘግቧል።

ዘይት ስኳርና መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች መጥፋታቸውና የኑሮ ውድነቱ የህዝቡን ተቃውሞ እንዳባባሰው ተገልጿል።

ከጨፌ ዶንሳ በ30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ከተማ የተነሳውን ተቃውሞ ለማስቆም የመንግስት ባለስልጣናት ዛሬ የጠሩት ስብሰባ በህዝብ ተቃውሞ መቋረጡንም የአካባቢው ነዋሪ ለኢሳት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በኢሉባቡር መቱ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ መደረጉ ተገልጿል።

የተቃውሞው መነሻ በግልጽ ባይታወቅም ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበረ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።