ኢሳት (ታህሳስ 17 ፥ 2009)
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ 14 ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ ሰኞ አስታወቀ።
14 ሰዎችን አሳፍሮ ከባቱ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረ የህዝብ ማመለሻ ተሽከርካሪ ቦራ ወረዳ ሶሪ ዴሊሳ ቀበሌ ሲደርስ ከቢሾፍቱ ወደ ባቱ ከተማ ከሚጓዝ ሲኖ ትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ አደጋው መድረሱን የፖሊስ መረጃን ዋቢ በማድረግ በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በዚሁ አደጋ ሾፌሩን ጨምሮ በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ በሙሉ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ የጭነት ተሽከርካሪው መንገዱን ስቶ ከአውቶቡስ ጋር መጋጨቱን የክልሉ ፖሊስ አመልክቷል።
ከአደጋው የተረፈው የሲኖ ትራክ አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት እንደሆነም ታውቋል። የኦሮሚያ ክልል በርካታ የትራፊክ አደጋዎች ከሚመዘገብባቸው ክልሎች መካከል ዋነኛው ሲሆን፣ ባለፈው አመት ብቻ ከ 4 ሺ በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ በሃገሪቱ መሞታቸውን የትራንስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ያረጁ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መበራከት፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የልምድ ማነስና የትራፊክ ምልክቶች በቦታው አለመኖር አደጋውን ከሚያባብሱት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ይገልጻል።
የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ኢትዮጵያ ካላት አነስተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር አንጻር እየደረሰባት ያለው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቋል።
ከ90 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባላት ኢትዮጵያ 700ሺ የማይሞሉ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን በቅርቡ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የተካሄደ ጥናት የመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ሶስት የእሳት ቃጠሎ አደጋዎች መድረሳቸውን ፖሊስ ሰኞ ገልጿል። ሶስቱ አደጋዎች በከተማዋ አሮጌው ፖስታ ቤት፣ ሃብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢና በጉለሌ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን አጥር አጠገብ መድረሱ ታውቋል።
በአሮጌው ፖስታ ቤት በደረሰው የእሳት ቃጠሎ አራት ሱቆች እንዲሁም በሃብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ ስምንት መኖሪያ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውድደማቸውን የአዲስ አበባ ከተማ የእሳት ማጥፊያና መቆጣጠሪያ መስሪያ ቤት ለመገኛኛ ብዙሃን ገልጿል።
በመድሃኒያለም ቤተ-ክርስቲያን አጥር አጠገብ በደረሰው ሌላ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ደግሞ ንብረታቸው የቤተክርስቲያኑ የሆኑ ሁለት የንግድ ሱቆች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለመረዳት ተችሏል። ፖሊስ የቃጠሎውን መንስዔ ለማወቅ ምርመራን እያካሄደ ሲሆን፣ በአደጋው 8 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ንብረት መውደሙን ፖሊስ አክሎ አስታውቋል።