ኢሳት (ሚያዚያ 25 ፥ 2008)
በድርቁ በተጎዱ ምስራቃዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የከፋ የረሃብ አደጋን ጨምሮ የሰዎች ሞት ሊያጋጥም እንደሚችል በቅድመ ረሃብ መከላከል ዙሪያ ትንበያ የሚሰጥ አንድ አለም አቀፍ ተቋም አሳሰበ።
ይከው በአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ተቋም ስር የሚገኘው የቅድመ ማሳሰቢያ ጥምረት፣ የድርቁ አደጋ በሰዎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየተባባሰ መምጣቱን እንደገለፀ ብሉም በርግ የዜና አውታር ማክሰኞች ዘግቧል።
የእርዳታ አቅርቦቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅትም ቢሆን በምግብ እጥረቱ የሚጎዱ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና በተለይ በምስራቃዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሞት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችልም አለም አቀፍ ድርጅቱ አስታውቋል።
በሃገሪቱ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ዙሪያ ሁለተኛ ትንበያውን ይፋ ያደረገው ይኸው ድርጅት በምግብ እጥረት ሳቢያ ልዩ እንክብካቤን የሚፈልጉ ህጻናት ቁጥር ባለፈው ወር ብቻ በ14 በመቶ ከፍ ብሎ መመዝገቡንም ገልጿል።
የተለያዩ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በሶማሊ ክልል ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ መልኩ እየተባባሰ መምጣቱንና በአካባቢው የከፋ የረሃብ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይኸው የከፋ የምግብ እጥረት እስከ መስከረም ወር ድረስ ይዘልቃል የሚል ግምት በመኖሩም ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን የአሜሪካው ተቋም በሪፖርቱ አመልክቷል።
በምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉ በርካታ ዞኖች በሁለት ተከታታይ የሰብል ወቅት ዝናብ ባለማግኘታቸው ምክንያት ድርቁ የከፋ ጉዳትን እያደረሰ መሆኑም ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለተረጂዎች መቅረብ ያለበት የምግብ እርዳታ ወቅቱን ጠብቆ ወደ ሃገሪቱ ባለምግባቱ ሳቢያ ድርቁ የከፋ ጉዳትን ሊያደርስ ይችላል ሲል በቅርቡ ማሳሰቡም የሚታወስ ነው።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው የእርዳታ ድርጅቶች የሚሰጡት ትንበያና ማሳሰቢያ የተጋነነ ነው በማለት ድርቁ የከፋ ጉዳትን አያስከትልም ሲል አስተባብሏል።
ለተረጂዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ በበቂ መጠን ባለመገኘቱ ምክንያትም የኢትዮጵያ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ወኪሎች በለጋሽ ሃገራት በመዘዋወር ድጋፍን እያሰባሰቡ የሚገኝ ሲሆን ከሚፈልገው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ መካከል 800 ሚሊዮን አካባቢ ብቻ የሚሆነው መገኘቱንም ለመረዳት ተችሏል።