በምርጫው ሰሞን ቀንሶ የነበረው የእህልና የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ተመልሶ እየናረ ነው

ሰኔ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግንቦት15 ምርጫ ከመካሄዱ 2 ሳምንት በፊት መንግስት ዋና ዋና የሚባሉ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ እንዲቀንስ ቢያደርግም ፣ ከምርጫው በሁዋላ ተመልሶ መውጣቱን ዘጋቢያችን ገልጿል።
ምስር በኪሎ ከ50 ብር በላይ፣ በርበሬ ከ120 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን የገለጸው ዘጋቢያችን፣ ዘይትና ስኳር ተመልሰው ከገበያ መጥፋታቸውን የስጋና የወተት ምርቶች እንዲሁም በሁሉም የእህል ዘሮች ላይ ጭማሪ መታየቱን ዘግቧል።
የመንግስት ሰራተኛውም ሆነ አብዛኛው ህዝብ እየታየ ባለው የዋጋ ንረት ምሬቱን እየገለጸ ሲሆን፣ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ እየጠየቁ ነው።
አንድ የመንግስት ሰራተኛ በወር የሚያገኘው ደሞዝ የቤት ኪራይ ከፍሎ ምግቡን በወጉ ለመመገብ እንደማያስችለው ለዘጋቢያችን ገልጿል። የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይሻሻላል ተብሎ ቢጠበቅም የሚሆን ነገር አልሆነም የሚለው ሰራተኛው፣
ስደትን እንደመፍትሄ ለመጠቀም እያሰበ መሆኑን ተናግሯል። እርሱ በሚሰራበት መስሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ቤተሰብ ያላቸው ሰራተኞች ህይወታቸውን እንዴት እንደሚገፉት እንቆቅልሽ እንደሆነበትም ተናግሯል።