ኢሳት (ታህሳስ 29 ፥ 2008)
በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ቀጥሎ የሚገኘው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በመንግስት ወታደሮች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በትንሹ 140 መድረሱንና ተቃውሞው አለመርገቡን በርካታ አለም-አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘገቡ።
ዳግም አገርሽቶ የሚገኘው ይኸው ተቃውሞ አርብ በምዕራብ ሃረርጌ በሚገኙ ሂርናና ጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ከተማ መቀስቀሱንና፣ የመንግስት ወታደሮችና ፖሊሶች እርምጃ መውሰዳቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ሁለተኛ ወሩን በያዘውና አለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ በሚገኘው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በመንግስት ወታደሮችና ፖሊሶች በትንሹ 140 ሰዎች መገደላቸውንና በርካታ ሰልፈኞችም ለእስር መዳረጋቸውን ቢቢሲ የተለያዩ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት የሟቾችን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥቦ ተቃውሞ በማሰማት ላይ ያሉ ሰዎችን ከሽብርተኛ ጋር ቁርኝት ያላቸው አድርጎ መግለጹ የዜና ወኪሉ አመልክቷል።
የመንግስት ታጣቂዎች እየወሰዱ ባለው እርምጃም፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራሮች ጨምሮ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንና ተቃውሞው እንደ 1977ቱ የምርጫ ተቃውሞ ጋር መጠነ ሰፊ ሆኖ መገኘቱንም መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የሂውማን ራይትስ ዎች ሃላፊዎች በበኩላቸው ባለፉት ስምንት ሳምንታት ውስጥ በጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎች በአግባቡ ለማወቅ አለመቻላቸውንና የተለያዩ አካላት በትንሹ 140 ሰዎች ስለመገደላቸው ማረጋገጣቸውን ይፋ አድርገዋል።
በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ተቃውሞና የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱት እርምጃ የሃገሪቱን ዘላቂ መረጋጋት አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል የሂውማን ራይትስ ዎች ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን ለእዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ተቃውሞን በሚያሰሙ ዜጎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አቁሞ ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን በአስቸኳይ እንዲፈታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አሳስቧል።
ሁለተኛ ወሩን በያዘው በዚሁ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በትንሹ 5ሺ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ መግለፁ የታወሳል።
ተቃውሞ በየእለቱ ቀጥሎ የሚገኝ በመሆኑም የሟቾችን ቁጥርና ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር በአግባቡ ማወቅ አስቸጋሪ መሆኑንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት አርብ ገልጸዋል።