በማስተር ፕላን ሰበብ የተነሳው ተቃውሞ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል፥ የመማር ማስተማር ሂደትን አስተጓጉሏል

ኢሳት (ታህሳስ 29 ፥ 2008)

ከቀናት በፊት ዳግም ያገረሸው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ አርብ በምዕራብ ሃረርጌ በምትገኘው የጭሮ ከተማና አካባቢዋ ቀጥሎ መዋሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በሌሎች አካባቢዎች የተወሰደው አይነት የመንግስት ታጣቂዎች እርምጃም በከተማዋ ተካሄዶ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው ተገልጿል።

ከቀናት በፊት በዚሁ በምዕራብ ሃረርጌ በምትገኘው የሂርና ከተማ ተቀስቅሶ የነበረው ተቃውሞ አለመብረዱንና አርብ በከተማዋና በዙሪያው ባሉ የገጠር መንደሮች ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ለመረዳት ተችሏል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ተቃውሞው በቁጥጥር ስር ውሏል ቢሉም በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የተቋረጠን ትምህርት ለማስቀጠል ድርድርን እያካሄዱ እንደሚገኝም ታውቋል።

ለእስር የተዳረጉ ተማሪዎች እንዲፈቱ ጥያቄን በማቅረብ ላይ የሚገኙት ተማሪዎች በትምህርት ተቋማት ውስጥ ሰፍረው የሚገኙ የመንግስት ታጣቂዎች ከግቢው ለቀው እንደወጡ ጠይቀዋል።

የዲላ፣ አዳማና ሌሎች ዩንቨርስቲ ተማሪዎች በመካሄድ ላይ ያለን የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በመቃወም ከቀናት በፊት ጥያቄን ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይሁንና የመንግስት ወታደሮች በወሰዱት የሃይል እርምጃ በትንሹ አራት ተማሪዎች የተገደሉ ሲሆን በዩንቨርስቲዎቹ የትምህርት ማስተማሩ ሂደትም መስተጓጎሉ ተነግሯል።

የመንግስት ታጣቂዎች መሳሪያ የታጠቁና የደበቁ አካላት አሉ በማለት በተለያዩ ከተሞች የቤት ለቤት ፍተሻን እያካሄዱ እንደሚገኝም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች ገልጸዋል።